አለም አቀፉን የጤና ደህንነት መርሀ ግብርን አስመልክቶ የተዘጋጀው የግምገማ ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ
የአለም አቀፍ የጤና ደህንነት የጥምር የውጭ ግምገማ (Joint External Evaluation) መርሀ ግብር ስብሰባ ሁሉንም ሴክተር መስሪያ ቤቶች በማሳተፍ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱ ተገለጸ፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር በእዚህ ሁሉንም ሴክተር መስሪያ ቤቶች፤ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጭምር ባሳተፈው ስብሰባ መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ በመገኘት ባስተላለፋት መልዕክት የጤና ሥራዎች የበርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በጋራ ተናቦ መስራትና መተጋገዝን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም ተቋማት ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት እንደነበረ ሁሉ አሁንም ቢሆን በጋራ ተባብረው እንዲሠሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ዶ/ር ጌታቸው አያይዘውም የጤናውን ስርዓት ማጠናከር የስብሰባው ዋና ዓላማ እንደሆነ አስረድተው ሀገር አቀፉ የጤና ደህንነት መርሃግብር ውጤታማ ይሆን ዘንድ የገንዘብ፤ የማቴሪያልና ቴክኒካል እርዳታ ለሚያደርጉ ተቋማት ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ምስጋቸውን አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ፈይሣ ረጋሳ የኢትዮጵያ የአለም አቀፉ ጤና ደንብ መርሀ ግብር ተጠሪ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት ቀደም ሲል በነበረው እና አሁን በተከናወነው ስብሰባ ላይ ሁሉም ሴክተሮች ተገቢውን እና በቂ መረጃዎችን በመስጠት ተሳትፎ ማድረጋቸውን አውስተዋል፡፡ ዶ/ር ፈይሣ አሁን በተከናወነው የጥምር የአለም አቀፍ የጤና ደህንነት የውጭ ግምገማ መርሀ ግብር ስብሰባ ላይ ዓለም አቀፉን የጤና ደንብ እሳቤዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ልዩ ልዩ ስራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህ የጥምር የአለም አቀፍ የጤና ደህንነት የውጭ ግምገማ መርሀ ግብር ስብሰባ ሀገራችን ያለችበትን ወቅታዊ አቅም ለማወቅ እና ቀጣይ የዓለም አቀፋን የጤና ደህንነት መርሃግብር ለመተግበር የሚቻልበትን ሁኔታዎች ለማጠናከርና ለማመቻቸት እገዛ ለማድረግ እንደሚረዳ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአዳማ ከተማ ለአራት ቀናት ያህል ሲካሄድ በቆየው በእዚህ የሀገሪቷ የጤና ደህንነት የራስ አቅም ግምገማ ስብሰባ ላይ ከተለያዩ መንግታዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተወጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡