አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በኢንስቲትዩቱ ተከበረ

የኢንስቲትዩቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ዳይሬክቶሬት የኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ከፍተኛ ሃላፊዎችና ሰራተኞች በተገኙበት የካቲት 30/2012 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አከበረ፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ለ109ኛ ጊዜ “I am Generation Equality ,Realizing Women’s Rights “፣ በሃገራችን ደግሞ ለ44ኛ ጊዜ ” የሴቶችን ደህንነትና መብት መከበር ለሰላማችንና ለህልውናችን መሰረት ነው፡፡” በሚል መሪ ቃል እተከበረ ይገኛል፡፡
ደ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበዓሉ የመክፈቻ ስነ-ስረዓት ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ችግሮችን በመቅረፍ ሴቶችን ያገናዘበ እኩልነት በማረጋገጥ መብታቸውን ከማስከበርም በላይ ሴቶችን ወደ አመራርነት የማምጣቱ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተለያዩ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸው በዝርዝር ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ ስነ-ስርዓት ወቅት አለም አቀፍ የሴቶች ቀን አመሰራረትና ታሪካዊ አመጣጥ በወ/ሮ ኑሪያ ዩሱፍ የሴቶች፣ወጣቶችና ህጻናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በጽሁፍ የቀረበ ሲሆን የሴቶች ቀን በመጀመሪያ በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ሀገራት መከበር መጀመሩን ፣ በጊዜ ሂደት በሌሎቹም የዓለም ሀገራት እየተከበረ መምጣቱን እንዲሁም በሀገራችን የሴቶች እኩልነት እንቅስቃሴዎች በይፋ መታየት ከጀመሩበት ጊዜ ሲታይ በርካታ ዓመታት መቆጠራቸውን እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተለያዩ ፖሊሲዎች ፣ ህጎችና ደንቦች ተቀርጸው ተግባራዊ እተደረጉ መሆናቸውን በጽሁፉ ተገልጻል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ትምህርት የሚሰጡ የተለያዩ ግጥሞች የቀረቡ ሲሆን የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የበዓሉ ተሳታፊዎች በርካታ ከሴቶች መብት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አንስተው ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ተገቢውን መልስ በመስጠት ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡