አንድ ጤና አስተዳደራዊ መዋቅር ረቂቅ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ
በኢትዮጵያ የአንድ ጤና (ዋን ሄልዝ) ባለድርሻ አካላት የምክክር ስብሰባ ከህዳር 25-27/2016 ዓ.ም. በተዘጋጀው የዋን ሄልዝ ሴክሬታሪያት ዘርፈ-ብዙ ሴክተሮች አስተዳደራዊ መዋቅር አደረጃጀት ረቂቅ ሰነድ ላይ በአዳማ ኤክሲክዩቲቭ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
የዚህ የምክክር መድረክ ዓላማ እ.አ.አ. በ2016 የተመሰረተውን የአንድ ጤና አስተባባሪ ኮሚቴ ባለፉት ሰባት አመታት ያከናወናቸውን አንኳር ተግባራትና ውስንነቶቹን በመመልከት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመዋቅር ክለሳ ወቅት በአዲስ መልክ የተቋቋመውን የሀገር አቀፍ የአንድ ጤና (ዋን ሄልዝ) ሴክሬታሪያት የመዋቅር አደረጃጀትና አሰራርን ለማሳለጥ በተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ላይ ተወያይቶ ለማዳበርና ተጨማሪ አሰተያየቶችን በግብአትነት ለማካተት እንዲቻል ለሚቀጥሉት ሶስት ተከታታይ ቀናት የሚመክር ይሆናል፡፡
በዚህ ዎርከሾፕ ላይ ቁልፍ የመንግስት ባለድርሻ አካላትና የልማት አጋሮች ተወካዮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ የዎርክሾፑ ታዳሚዎች ከግብርና ሚኒስቴሪና ተጠሪ ተቋማት፤ የጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም ከሆነው የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ባጠቃላይ 45 ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
በዎርክሾፑ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸው የሚከተለውን አንኳር ነጥብ አንስተዋል፡፡
በጊዜያዊነት የዋን ሄልዝ ሥራን ይመራ የነበረው ስቲሪንግ ኮሚቴ ባደረገው ጥረት ዘላቂነት ወደ ሚኖረው የኢንተር ሚኒስቴሪያል ታስክ ፎርስ ( Inter-ministerial task force) አመራር ሰጪነትና በቋሚ ሲቪል ሰረቫንት የሚተዳደር ቢጋር (TOR) አማካኝነት የዕለት ተዕለት ሥራውን የሚያከናውንበት ሴክሬታሪያት ላይ የቀረበውን ረቂቅ ሰነድና ፕሮፖዛል እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሰነዱን እንዲያዳብሩት በማስገንዘብ ይህንን ዎርክሾፕ ላዘጋጁት የኮሚቴ አባላትና አጋር ድርጅቶችን በራሳቸውና በኢንስቲትዩታቸው ስም አመስግነዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የዋን ሄልዝ አስተባበሪ ኮሚቴ ያለፉት ሰባት አመታት ክንውኖችን በተመለከተ በዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ የቀድሞ ዋን ሄልዝ አስተባባሪ ኮሚቴ ስብሳቢ በኩል የሚከተሉትን ዋና ዋና ስራዎች ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡
የአንድ ጤና (ዋን ሄልዝ) ስተራቴጂክ ዕቅድ ሰነድ ስለመዘጋጀቱ፤ ትኩረት የሚሹና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የእንስሳት ነክ በሽታዎች ልየታና ቅደም-ተከተል በማወጣት የመከላከልና መቆጣጠር ስትራቴጂ ስለመቀረፁ፤ የፈርጀ ብዙ ሴክተሮች የጤና ችግሮችና ወረርሽኞችን የመመሪመሪያና የመቆጣጠሪያ የተለያዩ መመሪያዎችን በማዘጋጀትና ለተከሰቱ ወረርሽኞች ምላሽ በመስጠት ረገድ እንዲሁም የሴክሬታሪያት አደረጃጀትን በተመለከተ ረቂቅ ሰነድ ጭምር ለዚህ ስብሰባ በማቅረብ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡