አገር አቀፍ የስርዓተ ምግብ ምርምር አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ እና ስነ-ምግብ ምርምር ዳይሬክቶሬት እና የብሔራዊ የስርዓተ ምግብ የመረጃ ማዕከል በጋራ በመሆን ከህዳር 29 እስከ ታህሳስ 1/2014 ዓ.ም የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምግብ እና የስርዓተ ምግብ ምርምር አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል እያካሄዱ ነው፡፡
የአውደ ጥናቱ ዋና አላማ በምግብና ስነ-ምግብ ዙሪያ የተሰሩ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች በአውደ ጥናቱ ላይ ቀርበው ለፖሊሲ እና ለፕሮግራም አውጪ አካላት መረጃ ላይ መሰረት ያደረጉ ግብዓቶችን ማቅረብ ነው፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ስነ -ስርዓት ወቅት እንደተናገሩት በአውደ ጥናቱ ላይ የምግብና የስርዓተ ምግብ እስትራቴጂ አፈጻጸምን በከፍተኛ ደረጃ ሊያግዙ የሚችሉ እንዲሁም የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለማሻሻል የሚረዱ ጥናቶች የሚቀርቡ መሆኑን፣ በተለይም በምግብና ስርዓተ ምግብ ዙሪያ ያሉትን በርካታ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በሃገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የህብረተሰብ የጤና አገልግሎት ስራዎችን እንዲሰራ ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው በምግብ እና ስነ- ምግብ ዙሪያ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ የምርምር ስራዎችን ተቋሙ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አውደ ጥናቱ ለተመራማሪዎች፣ለፖሊሲ እና ፕሮግራም አውጪዎች በመረጃ ግበዓትነት የሚያገለግሉ በርካታ የጥናት ውጤቶች እንደሚገኙ፣እንዲሁም ለምግብና ስርዓተ ምግብ እስትራቴጂ አፈጻጸም ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ መረጃዎች እንደሚቀርቡ ከአውደ ጥናቱ አስተባባሪዎች ማወቅ ተችሏል፡፡
የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣በምግብና ስነ-ምግብ ላይ የሚሰሩ የአለም አቀፍና የሀገር አቀፍ አጋር አካላት፣ የፖሊሲ እና የፕሮግራም አውጪ አካላት በአጠቃላይ ከ150 በላይ የሚሆኑ የጉባኤው ታዳሚዎች በአውደ ጥናቱ በመሳተፍ ላይ ያሉ ሲሆን ከ65 በላይ የምርምር ውጤቶች እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡