ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮሌራ በሽታ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመከላከል ይቻል ዘንድ የምታደርገው ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደነቀ፡፡
ኢትዮጵያ የኮሌራ በሽታ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመከላከል የምታደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ፍሬያማ ሆነው በመገኘታቸው አለም አቀፉ ማህበረስብ ዘንድ አድናቆትን አገኘች፡፡
በፈረንሳይ አነሲ ከተማ በመከናወን ላይ በሚገኘው በአመታዊ ዘጠነኛው አለም ዓቀፍ የኮሌራ መከላከል ግብረ-ሀይል ኮንፍረንስ (9th Annual Meeting of the Global Task Force on Cholera Control) ላይ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ የኮሌራ በሽታ ለመከላከል የምታደርገው ልዩ ልዩ ተግባራት ጥሩ ምሳሌ እና አርአያ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በዚሁ ኮንፍረንስ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት በአሁኑ ወቅት የኮሌራ በሽታ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለበትን ሁኔታና ባለፉት ሁለት አመታት የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራትን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጵያ ኮሌራ በሽታ ለመከላከል ያደረገችው እንቅስቃሴ ጎልቶ በመውጣቱ ለሌሎች ሀገራት ልምድና ተሞክሮዋን በኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በኩል አካፍላለች፡፡
በኮንፍረንሱ ላይ ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን ከማቅረቧም በላይ የኮንፍረንሱ አወያይ በመሆን ተመርጣለች፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አመታት በበርካታ ችግሮችና ወጀቦች መካከል ያለፈች ቢሆንም በጤናው ዘርፍ በተለይ የኮሌራ በሽታን ለመከላከል ብሎም የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችና ጠባሳዎችን ለማስቀረት ይቻል ዘንዳ በርካታ አመርቂ ስራዎች መከናወናቸው ለኮንፍረንሱ ታዳሚዎች በዝርዝር ቀርቧል፡፡
የኮሌራ በሽታን ለመታደግ ይቻል ዘንድ ቀደም ሲል በአለም ጤና ድርጅት በተዘጋጀው በ75ኛው የአለም ጤና ስብሰባ ( 75th World Health Assembly ) ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሠ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር በተገኙበት ላይ የአምስት አመት ዘርፈ ብዙ የኮሌራ እስትራቴጂ ፕላን የፀደቀ ሲሆን በቀጣይም ለሀገራችን የ6.8 ሚሊዮን ኮሌራን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት እርዳታ እንደሚገኝ ለማወቅ ተቸሏል፡፡ በመሆኑም ይህንኑ ክትባት ሀገራችን በቅርቡ ተረክባ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ክትባቱን እንደምታዳርስ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አለም ዓቀፉ የኮሌራ መከላከል ግብረ-ሀይል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፤ ልዩ ልዩ የተባበሩት መንግስታት ተቋማትን እንዲሁም በመስኩ በርካታ ምርምርና ጥናቶችን የሚያከናውኑ አጋር ድርጅቶችን አሰባስቦ የያዘ ኔትዎርክ ነው፡፡