ኢትዮጵያ የ 2030 የጤና ግቦችን አፈጻጸም የሚገመግም ከፍተኛ የዉይይት መድረክ አዘጋጀች

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የዘላቂ ግቦች( SDG) ስኬት ለመገምገም የሚያሰችል ከፍተኛ የምርምር ዉጤት ይፋ ማድረግያ መድረክ ታህሰስ 14/2018 ዓ.ም በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ተካሂዷል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸዉ ቶሌራ ሲሆኑ፤ ይህ ሰፊ ጥናት የተከናወነዉ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት መሪነት ከአፍሪካ የህዝብ ጤና እና ምርምር ማዕከል፤ ከማኒቶባ ዩኒቨርሲቲ፤ ከለንደን የንጽህና እና ትሮፒካለ ሜዲሲን ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር ነዉ፡፡
መድረኩ ላይ ዶ/ር አደራጀዉ መኮንን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የጤና ስርዓት ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳያሬክተር የ“countdown to 2030” ሀገራዊ የትብብር ጥናት ዋና ዋና ዓላማዎች ፤ የምርምር ዘዴዎች እና የጥናቱን ሂደቶቸ ለተሳታፊዎች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በዕለቱ በተከሄዱ የዉይይት ክፍለ ጊዜያት የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ጤና አገልግሎት አፈጻጸምን ፤ የመደበኛ የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓትን እና በተለያዩ ዘርፎች ቅንጅት የጤና ስርዓቱን ማጠናከር በሚቻልባቸዉ ሁኔታዎች ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡ አቶ አሸንፍ ታደለ በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪ የእናቶችን እና የጨቅላ ህጻነት ጤና አገልግሎት አፈጻጸምን አስመልክቶ ጥናታዊ ጹሁፍ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ባለሙያዎቹ የሰዎችን ህይወት ለመታደግ ትክክለኛ መረጃ ያለዉን ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመደበኛ የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓት ላይ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤ ይህም ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት የተሻለ ዉሳኔ ለመስጠት ያለዉን ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡ በሌላ በኩል አቶ ገረመዉ ጎንፋ በተለያዩ ዘርፎች ቅንጅት የጤና ስርዓቱን ማጠናከር የሚያስችሉ የምርምር ግኝቶችን አቅርበዋል፡፡
ከቀረቡት ጥናቶች በኋላ ከተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ከጤና ሚኒስቴር የመጡት ዶ/ር ሙሉቀን አራጋዉ እና ዶ/ር አባሰ ሀሰን እንዲሁም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸዉ ቶሌራ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የ2030 የልማት ግቦችን ለማሳካት በመጨረሻዎቹ አምስት ዓመታት ዉስጥ በምትገኝበት በዚህ ወቅት ይህ የምክክር መድረክ እንደ ትልቅ መገምገምያ ተወስዷል፡፡ተሳታፊዎቹ የቀረቡ የምርምር ግኝቶች ወደ ተግባራዊ ፖሊሲ በመቀየር ረገድ ሰፊ ዉይይት ያደረጉ ሲሆን መድረኩም የጤና ስርዓቱን ክፍተቶች በመለየት ለቀጣይ ስራዎች አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡