ኢንስቲትዩቱ ለክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በትላንትነው ዕለት ከኢንስቲትዩቱና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (ማኢሕጤኢ) የስራ አመራር ቡድን ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ገልፀዋል።
“ማኢሕጤኢ ባለው አነስተኛ የፋይናንስ አቅምና የሰው ሃይል እያደረገ ያለው የምርምር ስራ ሊደነቅና ሊበረታታ የሚገባው ነው። በምርምር ዘርፉ፣ በሕብረተሰብ ጤና፣ በሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ አስተዳደርና በመረጃ አስተዳደር ላይ የካበተ ልምድ ያለው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዉጤታማ የሆነ ድጋፉን ማድረግ ከመቻሉም በላይ ልምድ ካላቸው የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎችም ልምድ በመቅስም ብዙ መማር ይቻላል፣” በማለት ዶ/ር ጌታቸው ተናግረዋል።
በዕለቱም ዶ/ር ጌታቸው ለማኢሕጤኢ ዋና ዳይሬክተር፣ በኢህጤኢ ስር ካለው የብሔራዊ የስርዓተ ምግብ የመረጃ ማዕከል (ኒፕን) ፕሮጀክት ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችና የዋይፋይ ኢንተርኔት ማገናኛ ራውተሮችን ያስረከቡ ሲሆን ኢንስቲትዩቱ ለምርምር የሚያስፈልጉ የቢሮ ዕቃዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን መደገፉን እንደሚቀጥል አስታወቀዋል፡፡
የማሕጤኢ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ለተደረገው ድጋፍ ልባዊ ምስጋናቸውን በኢንስቲትዩታቸው ስም ገልጸው፣ “ማኢሕጤኢ ከፌዴራሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር ያለው የስራ ቁርኝት በእጅጉ ተጠቃሚ ነው። የተደረገልን ድጋፍ በስራችን እንድንበረታታ ከማድረጉም በላይ ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው፣” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።
ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ፣ የአካ/ጤናና/ ተላላፊ ያል/በሽ/ም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በዕለቱ ወደፊት ኢንስቲትዩቱ ለማኢጤኢ የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። “እንደ ኮምፒዩተር፣ ሰርቨርና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና የመሳሰሉት እገዛዎች በቀጣይም በብሄራዊ የስርዓተ ምግብ የመረጃ ማዕከል(ኒፕን) ፕሮግራም የድጋፍ መጠየቂያ ጽሁፍ አጻጻፍ ዘዴና (ግራንት አጻጻፍ) የመረጃ አስተዳደር ስልጠናዎችም በቅርብ ይሰጣሉ፣” በማለት አስታውቀዋል ።
ዶ/ር ስናፍቅሽ አየለ በማኢሕጤኢ የጤና ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርም ስለኢንስቲትዩታቸዉ የስራ እንቅስቃሴ ለአመራር ቡድኑ ገለጻ አድርገዋል። ዳይሬክተሯ፣ በሶስት ዳይሬክቶሬት የተዋቀረው ኢንስቲትዩት፣ በሰባት ዞኖችና በሶስት የወረዳ መስተዳድሮች ስር ያለውን ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን የክልሉን ህዝብ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።