ኢንስቲትዩቱ በጦርነቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ
March 8, 2022
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጦርነቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸዉ ለተፈናቀሉ ዜጎች የ5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች የተሰበሰቡ ግምታቸው ከ120 ሺህ ብር በላይ የሆኑ አልባሳና የምግብ ግብዓቶችን ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ይህንንም ለብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሺን አሰረክቧል፡፡
በርክክቡ ዕለትም የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሸነር አቶ ምትኩ ካሳ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስቀድመው በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋ በርካታ ዜጎች በመፈናቀላቸው ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ለወገን ደራሹ ወገን ነዉ በማለት ከባለ ሀብቶች፣ ከህብረተሰቡና ከትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፓራ ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ድጋፍ እየተደረገላቸዉ መሆኑን ገልጸው አሁን ባሉበት ደረጃም ችግሩን መቋቋም በመቻላቸው እየተደረገ ላለው ድጋፍ ሁሉንም አካል አመስግነዋል፡፡
በቦታው የተገኙት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክትር ዶ/ር ጌታቸዉ ቶሌራ እንደገለጹት ለተጎጂ ወገኖች ሰራተኛውን በማስተባበር ወደ 4 ጊዜ ድጋፍ መደረጉን እና ከሰራኞች ክበብ 5 ሚሊየን ብር ለድጋፉ ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ሀገራችን ከገጠማት ችግር በአሸነናፊነት እየተወጣች በመሆኑ በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ ባለው አቅም ድጋፉን እንደሚቀጥል ገልጸው የተደረገውን ድጋፍ በድርጅቱ ስም ለህዝባችን እንድታደርሱልን ሲሉ በትህትና ጠይቀዋል፡፡
እንደሚታወቀው በቅርቡ ኢንስቲትዩቱ ለመከላከያ ሰራዊት የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ነተመሳሳይ ሰራተኞቹ ደግሞ የአንድ ወር ደሞዛቸውን መስጠታቸው የሚታወስ ነው።