ኢንስቲትዩቱ ከቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ዴሊቨሪ ሜካኒዝም ላይ ስልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት ፎር ግሎባል ቼንጅ (Tony Blair Institute for Global Change [TBI]) ጋር በመተባበር የሕብረተሰብ ጤና ስራ አመራር የአቅም ግንባታ ፕሮግራም አካል ከሆነው አንዱ የዴሊቨሪ ሜካኒዝምስ ስልጠና ለኢንስቲትዩቱ አመራር አባላት ከሰኔ 14-15/2016 ዓ.ም ሰጠ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ፣ ይህ ስልጠና ኢንስቲትዩቱ የሚያከናዉናቸው ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ በይበልጥ አጠናክሮ በመፈፀም የሚጠበቀውን ውጤት በአጭር ጊዜ ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይም በየደረጃው ለሚገኙ ሁሉም የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በአዲሱ አደረጃጀት 37 ተግባራትና ኃላፊነቶችን ይዞ በ5 የስራ ዘርፎች ተደራጅቶ ተልዕኮዉን ለመተግበር እየሰራ ይገኛል።
ይህ የዴሊቨሪ ሜካኒዝም ስልጠና ኢንስቲትዩቱ ሀገራዊ ሪፎርምን ተከትሎ የተገበረውን የአደረጃጀት ለውጦችና የተልዕኮና ግብ ማሻሻያዎችን ከሚጠበቁ ውጤቶች ጋር ለማስተሳሰር እንዲቻል እና የስራ ኃላፊዎች እና መሪዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ውጤት ማምጣት እንዲችሉ የአቅም ግንባታ፣ ቅንጅታዊ አሠራር እና ትብብር በማሳደግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ እና ተናቦ መስራት የሚያስችላቸውን አቅም እንዲያጐለብቱ ያግዛል።
በኢንስቲትዩቱ የዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አማር ባርባ እንዳብራሩት ስልጠናው የኢንስቲትዩቱ የስራ አመራር አባላት የዴሊቨሪ ሜካኒዝምስ ፅንስ ሀሳብና አሰራር በመረዳት እና በመተግበር ተቋማዊ የአሰራር ስርዓት እና አቅም በማሳደግ ተቋማዊ ዓላማዎችና ግቦችን ማሳካት የሚችሉበት እንደሆነ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት የጤና ፕሮግራሞች ሲኒየር ማኔጀር ዶ/ር ብሩክ ተሾመ በስልጠናው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፡ የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ላለፉት 10 ዓመታት በስትራቴጂና በፖሊሲ ቀረጻ፣ እንዲሁም የውጤታማ አሰራር ዝርጋታ እና በቴክኖሎጂ ዙሪያ ለተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ተቋማት የድጋፍና የማማከር አገልግሎት ሲሠጥ ቆይቷል። ይኽ ሥልጠና በጤና ተቋማት አቅም ግንባታ ፕሮግራም የተሰጠ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን (EPHI) ፍላጎት ያገናዘበና አቅሙን በማጎልበት በአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕዩን በውጤታማነት አሠራር እንዲያሳካ የሚያግዝ ነው። የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ተመሳሳይ ሥራዎችን በናይጄሪያ፣ በአፍሪካ ሲዲሲ እንዲሁም በምዕራብ አፍሪካ የጤና ድርጅት (WAHO) ሲያከናውን ቆይቷል።