ኢንስቲትዩቱ ከክልል ጤና ቢሮ ተወካዮች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
ለጤና ላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት የሚውሉ የናሙና እና የውጤት ምልልስ አገልግሎት ከመልካ ምድር አቀማመጣቸው የተነሳ ለትራንስፖርት አገልገሎት እና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ተደራሽ ባልሆኑባቸው አከባቢዎች አማራጭ የተቀናጀ የናሙና ምልልስ እና ውጤት የማድረስ አማራጭ ዘዴ (Alternative Integrated specimen transportation and result delivery mechanism) ስራ ላይ እንዲውል ህዳር 5/2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልል ጤና ቢሮ ተወካዮች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
ከፍተኛ የምርመራ ቴክኖሎጂ የሚጠይቁ የጤና ላቦራቶሪ መመርመሪያ መሳሪያዎች ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የምርመራ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተቀናጀ የናሙና ቅብብሎሽ ስርአት በአገር አቀፍ ደረጃ ተዘርግቶ የናሙና ቅብብሎሹን ተግባራዊ ለማድረግ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ አገልገሎቱ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል ለኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በኮንትራት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከመልካ ምድር አቀማመጣቸው የተነሳ ለትራንስፖርት አገልገሎት እና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ተደራሽ ባልሆኑባቸው አከባቢዎች አገልገሎቱን በተጠናከረ መልኩ ለመስጠት አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ አማራጭ የናሙና ምልልስ እና ውጤት ማድረስ ዘዴ (Alternative Integrated specimen transportation and result delivery mechanism) ስራ ላይ እንዲውል የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአሰራር መመሪያዎችን ተግባራዊ ለመድረግ ከክልል ጤና ቢሮ እና ከክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች እና ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡ ሲሆን፣ ውይይቱንም በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይረክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እዳስገነዘቡት፣
የተቀናጀ የላቦራቶሪ ናሙና ምልልስ እና ውጤት የማድረስ አገልግሎት ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች አገልግሎቱን በተጠናከረ መልኩ ለመስጠት ይህ አማራጭ የአገልገሎት ዘዴ ያለው ጠቀሜታ እጅግ የጎላ ስለሆነ፣ የክልል ጤና ቢሮዎች ለዚህ ስራ ተግባራዊነት ትልቁን ሚና እዲጫወቱ መልክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ አያይዘውም ለዚህ አገልግሎት የተመደበውን በጀት በውሉ መሰረት ስራ ላይ እንዲውልና የተሻለ የናሙና እና ውጤት ቅብብሎሹን እንዲጠናከር መልክዕት አስተላልፈዋል፡፡ አተገባበሩን በተመለከተም የመግባቢያ የውል ሰነድ ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት በክልል ተወካዮች እና በኢንስቲትዩቱ መካከል ተፈራርመዋል፡፡