ኢንስቲትዩቱ የግማሽ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው
በኢንስቲትቱ የእቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የተቋሙን የ2013 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ከጥር 27 እስከ 29/2013 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ዋና ዳይሬክተር፣ ም/ዋና ዳይሬክተሮች እንዲሁም ሁሉም የማኔጅመንት አባላትና የቡድን አስተባባሪዎች በተገኙበት ግምገማ በማካሄድ ላይ ነው፡፡ ደ/ር ኤባ አባተ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በግምገማ መድረኩ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት ባደረጉት ንግግርእንደገለጹት በዓለም አቀፍ እና በሃገራችን ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ ብሎም ፖለቲካዊ ችግር የፈጠረውን ዓለም አቀፍ የኮሮና ወረርሺኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በርካታ ሚሊየን የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጀርባ በመያዝኢንስቲትቱ ከማንኛውም ተቋም በበለጠ ግንባር ቀደም በመሆን በርካታ ስራዎችን መስራቱ ሁሉም የሚያውቀው ሃቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ወረርሽኙን ከመከላከል ጎን ለጎን ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ተልዕኮ ከመወጣት አንጻር ምን ድረጃ ላይ እንደሚገኝ፣የነበሩ ጥንካሬዎች፣የታዩ ክፍተቶች እና በቀጣይ መሰራት ስላለባቸው ጉዳዮች መፈተሽ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ 2013 ዓ.ም ከመጠናቀቁ በፊት የሚቀሩትን ጥቂት ወራት ያልተከናወኑ ወሳኝ ሰራዎች እንዲተገበሩ ይህ የግምገማ መድረክ ከፍተኛ ሚና እንዲሚኖረውም ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ተናግረዋል፡፡ዳይሬክቶሬቶቹ ከኢንስቲትዩቱ እና ከስራ ክፍላቸው እቅድ አንጻር አፍጻጸማቸውን በጽሁፍ በማቅረብ ላይ የሚገኙ ሲሆን ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት ሰፊ ግምገማ እና ውይይት የሚካሄድ መሆኑን ከመድረኩ አስተባባሪዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡