ከእንስሳት ወደ ሰዉ የሚተላለፉ፣ ዞኖቲክ በሽታዎችን ለመከላከል ለመቆጣጠር በጋራና በትብብር መስራት ያስፈልጋል

ከእንስሳት ወደ ሰዉ የሚተላለፉ ዞኖቲክ በሽታዎች (Zoonotic Diseases) ላይ ስልጠና በተሰጠበት ፕሮግራም ላይ ተገኝተው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ እንዳሉት ከእንስሳት ወደ ሰዉ የሚተላለፉ ዞኖቲክ በሽታዎች ላይ ከዚህ በፊት ሲሰጠው ከነበረው ትኩረት፣ ስራና አመለካከት በበለጠ በሽታው በማህበረሰቡ ላይ ጉዳትና ሞት እንዳያስከትል በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ጤና ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው መ/ቤቶች እያደረጉ ካሉት የስራ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ከሚመለከታቸው አካላትና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
የዞኖቲክ በሽታው ምንነትና የሚያደርሰውን ጉዳት ለማሕበረሰቡ እንዲያሳውቁና እና ሕብረተሰቡም በሽታውን መከላከል እንዲችል ለጤና መረጃና ምክክር ባለሙያዎች እንዲሁም ለህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች ስልጠናው መሰጠቱ የበሽታው ስርጭት እንዳይስፋፋና ማህበረሰቡም ወቅታዊ መረጃውን እንዲያገኝ የሚያግዝ እንደሆነ አንስተው ማህበረሰቡም የቤት እንሰሳዎችን በሚያሳድግበት ወቅት ጤንነታቸውን በመጠበቅና አስፈላጊውን ክትባት እንዲያገኙ በማድረግ ማሳደግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ዶ/ር ተገኔ አክለውም ስልጠናውን የወሰዱት የጤና መረጃና ምክክር ባለሙያዎችና የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ማህበረሰቡን በማስተማርና የበሽታውን ስርጭት በመልከላከሉ ረገድ የስራቸዉ አካል አድርገዉ እንድሰሩ በማለት አሳስበው ስልጠናውን በትብብር ላዘጋጁት ለJohn Hopkins University (JHU) ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ስልጠናው ዋና ዋና Zoonotic Diseases በሚባሉት የእብድ ውሻ በሽታ (Rabies)፣ አባሰንጋ በሽታ (Anthrax)፣ ውርጃን በሚያስከትል በሽታ (Brucellosis)፣ በወፍ ዝርያዎች ላይ የሚከሰት በሽታ (High Pathogenic Avain Influenza) እና በስምጥ ሽለቆ ውስጥ የሚከሰት በሽታ (Rift Valley Fever) ዙሪያ ስልጠናው ተሰጥቷል።
በስልጠናው ላይ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የጤና መረጃና ምክክር ባለሙያዎች እና የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች እንዲሁም ስልጠናውን በመስጠት ደግሞ የJHU ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።