ከደቡብ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ መሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠናን ያጠናቀቁ 32 የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጣቸው።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ከደቡብ ብሔር፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሰት ከተለያዩ ወረዳዎች ተወጣጥተው በሶስት ዙር መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና (Frontline-FETP) ላጠናቀቁ 32 የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ህዳር 5/2015 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ የእውቅና ሰርተፍኬት ሰጠ፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክር በምረቃ ስነ ስርዐቱ ላይ እንደገለጹት ስልጠናው በሀገሪቱ በሚገኙ ወረዳዎች በሙሉ ቢያንስ አንድ አንድ ባለሙያ መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና እንዲያገኝ ማስቻል ሲሆን ባሁኑ ወቅትም በሀገር ደረጃ ዕቅዱን 75 በመቶ ማሳካት ተችሏል።አያይዘውም በአንዳንድ ክልሎች የሲዳማ ክልልን ጨምሮ የዕቅዱ አፈጻጸም ወደ መቶ በመቶ ተጠግቷል።
” ይህን ስልጠና ያጠናቀቃቹህ ባለሙያዎች የመጣቹህበትን ክልል፥ ወረዳና ዞንን ብሎም በአጠቃላይም ሀገራችሁንና እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ የሚከሰትባቸውን አጎራባች ሀገራትን ማገልገል ይጠበቅባችኋል፥” በማለት ባለሙያዎቹ የተጣለባቸውን ሀላፊነት አቶ አስቻለው አስረድተዋል።
የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው እንደተናገሩት ስልጠናውን የወሰዱ ባለሙያች ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ወቅቱ በሚጠይቀው የመረጃ ልውውጥ መሰረት የተለያዩ በሽታዎችን ቀድሞ በመለየት በፍጥነት ሪፖርት በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ነው።
አቶ ጃፈር ከዛሊ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር መዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ ስልጠናው በሶስት ዙር መሰጠቱን የገለጹ ሲሆን መሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀት፣ የቅኝት መረጃን (Surveillance data) በመጠቀም ወረርሺኝ በአንድ አካባቢ ቢከሰት ቶሎ በመለየት ሪፖርት የማድረግ ምላሽ የመስጠትና የመከላከል ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና ለባለሙያዎቹ በሶስት ዙር በስፋት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ባለሙያዎቹ መፍትሄ የሚሹ ያሏቸውን በስራ ላይ የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች፥ የአደረጃጀት ሁንታዎችንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸው በመድረክ መሪዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።