ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ሆኖ መቀጠሉ ተገለጸ
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል (PHEOC) የኮቪድ-19 የ6 ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ 6 ወራት የእቅድ ዝግጅት ከየካቲት1 እስከ 3/2015ዓ.ም በአዳማ ከተማ አውደ ጥናት በማካሄድ ላይ ነው፡፡
የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ የኮቪድ-19 አሁናዊ ሁኔታ እና ምላሽ አሰጣጥ ግምገማ በማድረግ ወቅቱን ያገናዘበ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራን ለመስራት የሚያስችል የእቅድ ዝግጅት ለማድረግ ነው፡፡
አቶ ሻምበል ሀቤቤ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የመረጃ ስርዓት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር እና የኮቪድ-19 ምላሽ ም/አስተባባሪ በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደገለጹት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን ላለፉት 3 ዓመታት የቀጠለ መሆኑንና ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ መደበኛው የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርና የጤና አገልግሎት አሰራር ስርዓት ለማስገባት ለ6 ወራት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ሻምበል አያይዘውም ያለፉትን 6 ወራት የስራ አፈጻጸም በመገምገም እና በአሁኑ ሰዓት የዓለም ጤና ድርጅት/WHO/ ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ሆኖ የቀጠለ መሆኑን በገለጸው መሰረት እንዲሁም የቫይረሱን ተለዋዋጭ ባህሪ ግምት ዉስጥ በማስገባት ለቀጣይ 6 ወራት ለሚከናወኑ ስራዎች እቅድ ክለሳ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የእቅድ ክለሳ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እየተዘጋጀ ያለው እቅድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን ከመደበኛው የሕብረተሰብ ጤና ቁጥጥርና የጤና አገልግሎት ስርዓት ጋር ለማቀናጀት እና ሀገራዊ የምላሽ ዝግጅት አቅምን በማጠናከር የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የሚያስችል መሆኑን አቶ ሻምበል ሀቤቤ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 የ6 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የኮቪድ-19 ወቅታዊ ሁኔታን ትኩረት ያደረገ በተለይም የአለም አቀፍ ጤና ደርጅት የትኩረት አቅጣጫ በስቀመጠው መሠረት በቀጣይ 6 ወራት የሚሰሩ ስራዎችን ዝርዝር ረቂቅ እቅድ በአውደ ጥናቱ ቀርበው እንደሚገመገሙ የአውደ ጥናቱ አስተባባሪዎች ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል፣ የኢንስቲትዩቱ ተለያዩ የስራ ክፍል እና የአጋር ድርጅት ባለሙያዎች በአውደ ጥናቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡