ወባና ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን እንዲሁም እንስሳት ነክ በሽታዎችን….

ወባና ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን እንዲሁም እንስሳት ነክ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰሩ ያሉ የምርምር ስራዎች በልዩ ትኩረት ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወባና ትኩረት የሚሹ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸምና በቀጣይ ለስድስት ወራት ተግባራዊ ስለሚደረጉ እቅዶች በአዳማ ከተማ የግምገማ አውደ ጥናት አካሄደ፡፡
በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በኢንስቲትዩቱ የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ውጤቶች የጤናውን ፖሊሲ፣ ፕሮግራሞች እና ስትራቴጂዎች ውሳኔ ተሰጥቶባቸው በተሻለመንገድ እንዲመሩ ለማድረግ የሚያስችሉ መረጃዎችን የማመንጨትና የማቅረብ ስራ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው አያይዘውም ወባና ትኩረት የሚሹ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት በአገር አቀፍ ደረጃ በወባ በሽታ ዙሪያ የተዋስያን መድኃኒት መላመድን፣ የመድኃኒት ፍቱንነትን፣ Malaria Molecular Markers Surveillance (MMMS)/የወባ ሞልኩላር ማርከርስ ቅኝት/፣ የወባ ጠቋሚ ቅኝት፣ የወባ ፈጣን መመርመሪያ፣ የወባ አስተላላፊ ትንኞች ዙሪያ እና ወባን ከመከላከልና መቆጣጠር እስከ ዘረመል ጥናትና ትንተና ድረስ ያለውን የምርመር ስራ በማካሄድ በርካታ ጥናቶች እና የምርምር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ በሽታዎች ላይ በተለይም በውሃና በአፈር ንክኪ የሚመጡ በሽታዎችን የመለየትና የመከላከል ብሎም የመቆጣጠር ስራዎችን የሚገመግሙ የምርምርና የቅኝት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን፣ ለዚህም በወላይታ ዞንተ ግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የጋሸሮ ፕሮጀክት ትልቁና ዋናው ማሳያ መሆኑን ተናግረው ከእንሰሳት ወደ ሰው የሚተላላፉ በሽታዎችን በሚገባ ለመከላከል ከሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ዳይሬክቶሬቱ በአለም አቀፍደረጃ በታወቁ ጆርናሎች ላይ በርካታ የምርምር ውጤቶችን ያሳተመ ዳይሬክቶሬት መሆኑን ም/ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ገረመው ጣሰው የኢንስቲትዩቱ ወባና ትኩረት የሚሹ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው እንደገለጹት በእቅድ አፈጻጸም ላይ የታዩ ጠንካራ ስራዎችን ለማስቀጠልና ክፍተቶችን በማስተካከል በቀጣይ 6 ወራት የተሻሉ የእቅድ አፈጻጸም ውጤቶችን ለማስመዝገብ እንዲሁም ከሌላ ተቋማት በዝውውር ወደ ዳይሬክቶሬቱ ለመጡ ባለሙያዎች የኢንስቲትዩቱን ዓላማና ተልዕኮ ለማስተዋወቅ አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
ዶ/ር ገረመው አክለውም፤ ዳይሬክቶሬቱ በወባ እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንቲሞሎጂ ምርምር ዲቪዥን ስር በወባና በወባ አምጪ ትንኝ ዙሪያ ለግማሽ ዓመቱ ታቅደው የነበሩትን የምርምርና የቅኝት ተግባራት ከፍተኛ የአፈጻጸም ዉጤት ማስመዝገቡን፣ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች እና እንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዲቪዥኖችም በተመሳሳይ መልኩ አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የማኔጅመንት አባላትና የዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች በአውደ ጥናቱ የተሳተፉ ሲሆን የምርምር መረጃዎችን የማከማቸት፣ አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም በተቋም መልካም አስተዳደር ዙሪያ ከሚመለከተዉ የተቋሙ የሥራ ክፍሎችእንዲሁም የዳይሬክቶሬቱ የተለያዩ ሪፖርቶችን በጽሁፍ ቀርበው ሰፊ ውይይት እና ግምገማ ከመካሄዱም በላይ በቀጣይም በቅንጅትና በመናበብ ስራዎች መከናወን እንደሚገባቸውና በኢንስቲትዩቱ የታቀዱ ተግባራትን በተዋረድ ሁሉም የየራሱን ድርሻ በመውሰድና በማቀድ ብሎም በማከናወን የተቋሙን ዓላማ ለማሳካት ከምንጊዜውም በላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡