ዓመታዊ የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች ብግርነት የዳሰሳ ጥናት የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው
በኢንስቲትዩቱ የባክቴሪያል፣ የፓራሳይቲክ እና እንሰሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ እና ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም ም/ዋና ዳይሬክተሮች በተገኙበት ዓመታዊ የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች ብግርነት Ani-microbial Resistance (AMR) የዳሰሳ ጥናት የምክክር መድረክ የካቲት 18 እና 19/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የምክክር መድረኩ ዋና ዓለማ ኢ.ኤ.አ በ2022/23 የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች ብግርነት የፕሮግራም ስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ለመገምገምና ለቀጣይ ስራዎች አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ነው፡፡
ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ በመድረኩ መክፈቻ ፕሮግራም ወቅት እንደገለጹት ቀደም ሲል በጤና ሚኒስቴር መመሪያ መሰረት የብሄራዊ የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች ብግርነት የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን እና ይህም በአለፉት ዓመታት የመድሃኒቶች ብግርነት መረጃዎች በሚገባ እንዲሰበሰቡ እንዲሁም ደረጃቸውን ለማወቅ ማስቻሉን፣ በተለይም የዳሰሳ ጥናቱ ግኝት የአገር አቀፍ ፖሊሲዎችን ለማስተካከል ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ የመድሃኒት ብግርነት ጥናት በግብዓትነት ማገልገሉን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው አሁን እየተካሄደ ያለው የጸረ-ተህዋስያን የመድሃኒት ብግርነት ጥናት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተጀመረ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው የቅኝት የሆስፒታሎችም ቁጥር መጨመሩንና የመድሃኒት ብግርነትን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለባለሙያዎች የተሻለ ግንዛቤ የመፍጠር ሰራ፣ በብሔራዊ እና በክልል ብሎም በዓለም ደረጃ ጠንካራ የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች ብግርነት ትብብር መፈጠሩን እና ለሆስፒታሎች የዓቅም ግንባታ፣ የቴክኒካዊና የግብዓት ድጋፍ እተደረገ መሆኑን እንዲሁም የመድሃኒት ብግርነት አንድ ጤናን የሚመለከት በመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ የዕለቱ መድረክ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ ዓለም አቀፍ የጸረ-ተህዋስያን መድሃኒቶች ብግርነት ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ባቀረቡት ጽሁፍ እንደገለጹት በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት በመድሃኒት ብግርነት ምክንያት በዓመት ሰባት መቶ ሺ ሰዎች እየሞቱ መሆኑንና በቀጣይ ተገቢውን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ካልተሰራ ኢ.ኤ.አ በ2050 በዓመት የሚሞተው ሰው 10 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ጥናቶች የሚያመለክቱ መሆኑን አቅርበዋል፡፡
የተለያዩ ሆስፒታሎች፣ የክልል ላቦራቶሪ ኃላፊዎች፣ የአጋር ድርጅት ተወካዮች እና የኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የስራ ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመድረኩ እተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ የጥናት ጽሁፎች እየቀረቡ ውይይት እየተካሔደባቸው ከመሆኑም በላይ በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች የጋራ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ከመድረኩ አስተባባሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡