ዕቅድን ማናበብ ስትራቴጂዎችና ግቦችን ለማሳካት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
የኢትጵዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዕቅድ፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት
ከመስከረም 21-23/2016 ዓ.ም ባዘጋጀው መድረክ የ2016 ዓ.ም ዕቅድን ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የማናበብ እና የማቀናጀት ስራ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን በመድረኩም ዕቅድን ማናበብ ስትራቴጂዎችና ግቦችን ለማሳካት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።
የኢንስቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር አማር ባርባ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት ዕቅድን ማናበብ ሃርሞናይዜሽን እና አላይንሜንት የሚባለውን ጽንሰ ሃሳብ መነሻ ያደረገ ተግባር ሲሆን ለጋሽ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን የተናጥል ተልዕኮ ይዘው ከማስፈጸም ይልቅ ሀገሪቷ ያስቀመጠችዉን የትኩረት አቅጣጫ ስትራቴጂዎችና ግቦችን ለማሳካት ሁሉም አካላት እንዲረባረቡ የሚያችል ነው፡፡ ይህም የተቋማትና ባለድርሻ አካላት ዕቅድ ባለመናበብ ምክኒያት ሊከሰት የሚችለውን ለሀገሪቱ የህብረተሰብ ጤና ልማት ስትራቴጂ ትኩረት አለመስጠት ያስቀራል፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገሪቷ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተያዘውን ስትራቴጂክ ዕቅድ በሁሉም ደረጃዎች የጋራ በማድረግ ለተፈጻሚነቱ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የዕቅድ፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ሞገስ በበኩላቸው ዕቅድን ማናበብ የሕብረተሰብ ጤና ስትራቴጂዎችና ተያያዥ የሆኑ የሥራ ማዕቀፎችን ለማጠናከር፣ በአጋር ድርጅቶች የሚመጡ ስራዎችን እና ዕርዳታዎችን ከሀገሪቱ ቅድሚያ የሚሹ የሕብረተሰብ ጤና ጉዳዮች፣ ስርዓቶች እና አሰራሮች ጋር በማናበብ የሀገር አቅም ለመገንባት፣ አላስፈላጊ የሀብትና የጊዜ መባከኖችን በማስቀረት የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተዋናዮች ተገቢውን ሁሉ እንዲፈጽሙ ከማስቻሉም በተጨማሪ የመተባበርየመተባበር ባህል በማጎልበት ዘለቀታ ያለው መናበብ በመፍጠር ለሀገሪቱ ቅድሚያ የሚሹ የህብረተሰብ ጤና ስትራቴጂዎች፣ አሰራሮችና ስርዓቶች ተግባራዊነት ከፍተኛ ጥቅም አንዳለው አመላክተዋል።
በመድረኩም ላይ የኢንስቲትዩቱ የ2016 ዓ.ም ዕቅድና ባለፈው ዓመት በየክልሉ ጤና ቢሮዎች እና የሕብረተሰብ ጤና ኢስቲትዮቶች ላይ የተካሄደው የተደረገው የግምገማ ውጤት የቀረቡ ሲሆን በነዚህም ላይ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ተሳታፊዎች በየዘርፋቸው በቡድን በመሆን ዕቅዳቸውን ይናበባሉ ።