የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስራዎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልገው ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዛሬው እለት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ቴክኒካል የትግበራ ቡድንን ይበልጥ በማጠናከርና በማደራጀት በተጠናከረ መልኩ ወደ ስራ በሚገባበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው የሀገር ቤትና አለም ዓቀፍ አጋር ተቋማት ጋር የጋራ ምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስራዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንዳ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የተቀናጀ እና የተናበበ እንቅስቃሴን እንደሚጠይቅ አስረድተው ለእዚህም የሁሉም ተቋማት ርብርቦሽ እና ተናቦ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ቀደም ይንቀሳቀስ የነበረው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ቴክኒካል የትግበራ ቡድን ከበፊቱ በበለጠ ተጠናክሮ የሚጠበቅበትን ስራዎች እንዲያከናውን ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡
በእዚሁ ስብሰባ ላይ በዶ/ር ያረጋል ፉፋ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መልሶ ማቋቋምና ሪዚሊያንስ ዳይሬክተር በሀገራችን በተከሰተው ልዩ ልዩ ግጭቶች ምክንያት ስላለው ሠብአዊ ምላሾችን በተመለከተ እና ዶ/ር ሚኪያስ ተፈሪ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ 19 ምላሽ ም/ዋና አስተባባሪ የኮቪድ 19 ምላሽ ላይ ምን ምን ምላሽ ላይ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ወቅታዊ መረጃዎችን አስመልክቶ እንዲሁም አቶ መስፍን ወሰን በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎችና ጤና ክስተቶች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክተር ሀገራዊ አጠቃላይ ወረሽኞችን አስመልክቶ እየጠከናወኑ ስላለው እንቅስቃሴዎች ገለጻዎች ያደረጉ ሲሆን የስብሰባው ተካፋዮች በቀረቡት ገለጻዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች አካሂደዋል፡፡