የህጻናት ህመምና ሞት ዋና ዋና መንስኤን አስመልክቶ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራ እና ትንተና ማዕከል ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ እና ከህጻናት ጤና እና ሞት መከላከልና ክትትል ጥናት (CHAMES Ethiopia) ፕሮጀክት ጋር በመተባባር በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት የህመም እና ሞት ዋና መንስኤዎች ምን ምን ናቸው የሚሉትን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሰኔ 7/2015 ዓ.ም በኢንስቲትዪቱ የስልጠና ማዕከል ውይይት አካሄደ፡፡
የውይይት መድረኩ ዋና ዓላማ የህጻናት ህመምና ሞት ዋና ዋና መንስኤዎች እና መፍትሄያቸውን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ግንዛቤ በማስጨበጥ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡
በህጻናት ጤና እና ሞት መከላከልና ክትትል ጥናት (CHAMES Ethiopia) ፕሮጀክት ድጋፍ አማካኝነት በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት የህመም እና ሞት ዋና ዋና መንስኤ ላይ የተካሄደ ጥናት በመድረኩ ቀርቦ ባለሙያዎቹ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡
ጥናቱ በምስራቅ ኢትዮጵያ በተለያዩ ሶስት ወረዳዎች በህጻናት ህመምና ሞት መንስኤ ላይ የተካሄደ ክትትል ሲሆን በጽንስ ጊዜ የምግብና የአየር መቆራረጥ፣ የነርቭ ዘንግ ክፍተት፣ በወሊድ ጊዜ የጨቅላ ህጻናት መታፈን ፣ ከክብደት መጠን በታች ሆኖ መወለድ እና ከጨቅላ ህጻናት በላይ እና ከአምስት በታች ያሉ ህጻናት ደግሞ የምግብ እጥረት ዋና ዋናዎቹ የሞት መንስኤዎች መሆናቸውን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡
በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት አንዱ ለህጻናት ሞት መንስኤ መሆኑንና በጨቅላ ወቅት ለሚከሰት ሞት ደግሞ በወሊድ ወቅት በሚከሰት መታፈን ችግር ጋር ተያይዞ በጀርም መመረዝና የሳንባ ምች ለሞት የሚዳርጉ ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውንም በጥናቱ ተብራርተዋል፡፡
ለችግሮቹ የሚወሰዱ መፍትሄዎችን በተመለከተ እናቶች ቅድመ እርግዝና ክትትል እና ቅድመ ወሊድ ክትትል እንዲያደርጉ እንዲሁም በእርግዝና ወቅት ያለ የአመጋገብ ስርዓት ማስተካከል እንደሚገባቸው ጥናቱ አጽንኦት የሰጠ ሲሆን የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠርን ደግሞ የጤና ተቋማት ክትትል ማድረግ እጅግ ተገቢና አስፈላጊ መሆኑን በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
በውይይቱ መጨረሻም የኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራ እና ትንተና ማዕከል፣ የጤና ሚኔስቴር፣ የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ እና የህጻናት ጤና እና ሞት መከላከልና ክትትል ጥናት (CHAMES Ethiopia) ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በመተባበር በተለያዩ የሚዲያ አግባቦች በመጠቀም ለህብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ በመፍጠር ችግሩን በቀጣይ መቅረፍ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡