የህጻናት ሞት መንስኤ ዙርያ ጥናቶች ተከናወኑ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል በሀሮሚያ ዮኒቨርስቲ ከሚካሄደው ከቻምፕስ ፕሮጀክት ጋር በመቀናጀት የህጻናት ሞት መንስኤ እና ደረጃ ጠቋሚ የሆኑ የጥናት ውጤቶችን ለባለደርሻ አካላት ያደረሰበትን ስብሰባ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አከናወነ፡፡
ዶ/ር አለምነሽ ኃይለማርያም በኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪና አስተባባሪ በስብሰባው መክፈቻ ላይ እንዳስገነዘቡት ማዕከሉ ለጤና ሥራዎች ግብአትና ለፓሊሲ ትግበራ እንዴት ጥቅም ላይ መዋል እንደሚቻል በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን የባለድርሻ አካላት ተሳትፎም እጅግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ስብሰባው የህጻናት ሞት መንስኤ እና ደረጃ ጠቋሚ የሆኑ የጥናት ውጤቶችን ለባለድርሻ አካላት ከማድረስ በተጨማሪ የጥናት ውጤቶችን ለፖሊሲ ፕሮግራም ግብአትነት ሊውሉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር የታወቀ ሲሆን አገር አቀፍ የሆኑ የጥናት ውጤቶችን አጠቃቀም ላይ የባለድርሻ አካላትን ልምድ ለማዳበርና ምክረ ሀሳቦችን ለማመንጨት ብሎም ዘመኑን የዋጀ የዳታ ቅመራና ዘዴዎችን በመጠቀም የፕሮጀክቱን የጥናት ውጤቶች ማቅረብ ላይ እንደሚያተኩር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በስብሰባው ላይ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ግኝቶች ቀርበው ውይይቶች ተካሂዶባቸዋል፡፡