የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማሕበረሰቡን የጤና ተግባቦት ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ ተገለጸ
የኢንስቲትዩቱ የቅኝትና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የሕብረተሰብ ጤና ተግባቦት ዲቪዥን ዓመታዊ የአፈጻጸም ግምገማና የ2017 ዓ.ም የእቅድ ዝግጅት መድረክ ከሐምሌ 18 እስከ 20/2016 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አካሄደ፡፡
የግምገማ መድረኩ ዋና ዓለማ በ2016 በጀት ዓመት በቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የሕብረተሰብ ጤና ተግባቦት ዲቪዥን እና በክልል የሕብረተሰብ ጤና ተግባቦትና የማህበረሰብ ተሳትፎ በኩል የተሰሩ ዋና ዋና ተግባራትን በመገምገም የነበሩ ክፍተቶችን የመለየት እና አቅጣጫ የማስቀመጥ እንዲሁም በ2017 ዓ.ም ውጤታማ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የሕብረተሰብ ጤና ተግባቦት ስራዎችን በመስራትና የማሕበረሰቡን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ክስተቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የጋራ እቅድ ለማዘጋጀት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ስራዎችን እንዲሁም ከሁሉም ክልል የጤና ቢሮዎች እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች የሕብረተሰብ ጤና ተግባቦትና የማህበረሰብ ተሳትፎ ባለሙያዎች እና ተወካዮች በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የሕብረተሰብ ጤና ተግባቦት ስራዎችን አስመልክቶ የተከናወኑ ተግባራትን በጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ሰፊ ውይይት እና ግምገማ በማድረግ የነበሩ መልካም ተሞክሮዎች፣ የታዩ ክፍተቶችንና መሰናክሎችን የመለየት ስራ ተሰርቷል፡፡
የቀጣይ በጀት ዓመት የጋራ እቅድ ተገምግሞ የተዘጋጀ ሲሆን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማሕበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እጅግ ወሳኝ መሆኑ በተቀመጡት የቀጣይ አቅጣጫዎች ትኩረት እና አጽንዖት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸው በውይይቱ ወቅት በስፋት ተገልጿል፡፡