የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀሙን ገመገመ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ፣ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የስራ ክፍል ሃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የብቃትና ሰዉ ሀብት አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ፣ የግዥና ፋይናንስ ስራ አስፈፃሚ እንዲሁም የፋይናንስ ባለሙያዎች በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ ከግንቦት 9-11/2016 ዓ.ም ተካሄደ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ እንደተናገሩት የግምገማ መድረኩ ዋና ዓላማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሰራነዉ ስራ ዉስጥ ምን ጥሩ ነገር ሰራን? ምን አስቀጥለን ምንስ ማሻሻል አለብን? ያሉን መልካምና ጠንካራ ጎኖች ምንድን ናቸው? ማስተካከል ያለብንና በቀጣይ አጠንክረን መስራት ያለብን ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች በመመለስ ለወደፊት እንዴት ከዚህ የተሻለ ዉጤታማ መሆን እንደምንችል ለመወያየት ያለመ ነው ሲሉ ገልፀዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ መጪውን የክረምት እና የዝናብ ወቅት ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችንና ድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ከአሁኑ አቅደንና ትኩረት ሰጥተን መነጋገርና መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በቅርቡ በተቋማችን የተደረገውን የመዋቅር መሻሻል እንዴት አድርገን ወደ ስራ እንገባለን? ሽግግሩ እንዴት መሆን አለበት? የሚለውን በጋራ በመወያየት ጥሩ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ተሳታፊዎች በንቃት እንዲወያዩ አደራ በማለትና መልካም የዉይይት ጊዜ ተመኝተዉ የግምገማ መድረኩን በይፋ ከፍተዋል።
በመቀጠልም የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል ስር የሚገኙ የስራ ክፍሎች ላለፉት ዘጠኝ ወራት የሰሯቸዉን ስራዎችና ያጋጠሟቸዉን ተግዳሮቶች በፅሁፍ ሪፖርት አቅርበዉ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ሰፊ ውይይትና ማብራርያ ተካሂዶባቸዋል፡፡ የብቃትና ሰዉ ሀብት አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ እና የግዥና ፋይናንስ ስራ አስፈፃሚ ከሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል ጋር በጋራ ስለሰሯቸዉ እና ወደፊትም አብረዉ ስለሚሰሯቸዉ ስራዎች ገለፃና ምክክር አድርገዋል።
በማስከተልም በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል ስር ያሉ የስራ ክፍሎች በቡድን በመሆን በቀጣይ ሊሰሯቸዉ ያቀዷቸዉን ዕቅዶች በድጋሚ በጥልቀት በማየት በተሳታፊዎች አስተያየት ተሰቶባቸዋል። ዉይይቱን የመሩት ም/ዋና ዳይሬክተሩ የስራ አመራርነትን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፅሁፍ አቅርበዉ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራርያ በመስጠት የተሻሻለውን መዋቅር በመተግበር ወደስራ መገባት እንዳለበትም አቅጣጫ ሰጥተውበታል፡፡
በመጨረሻም ሁሉንም የስራ ክፍሎችና የዉይይት ተሳታፊዎችን እንዲሁም የመድረኩን አዘጋጆች አመስግነዉ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ስራ በመስራት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ክስተቶችን መከላከልና መቆጣጠር እንደሚገባ በማሳሰብና የተሳካ የስራ ጊዜ እንዲሆን ተመኝተዉ የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡