የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ባለሙያዎች የተከታታይ የባለሙያዎች ስልጠናን መሠረት ባደረገ የፊልድ ኢኘዲምሎጂ ስልጠና ተመረቁ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት እና የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ የስልጠና ማዕከል በጋራ ባካሄዱት የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ((Frontline Epedemology Training) (FETP)) ያጠናቀቁ 29 የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ጥር 28/2016 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጣቸው።
ባለሙያዎቹ የተውጣጡት ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ ከሐረር እና ከሶማሌ ክልሎች ከሚገኙ ወረዳዎች ነው። ስልጣኞቹ ሦስት ግዜ በተካሄዱ ስልጠናዎች የተገኙ ሲሆን፣ ይህ የመጨረሻውና በየወረዳቸው በመሄድ የሰሯቸውን ስራዎች ያቀረቡበት ነው።
ይህ የተከታታይ የባለሙያዎች ስልጠና (CPD) ላይ መሠረት ያደረገ ስልጠና ሲሆን ይኸኛው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን የመጀመሪያው በአዳማ ከተማ ከኦሮሚያ ለተውጣጡ ባለሙያዎች ተሰጥቷል።
የእውቅና ምስክር ወረቀቱ በተሰጠበት ዕለት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ነኢማ ዜኑ፣ የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ጤና ቢሮ ተወካይ ኢብራሒም አብዱልአሚድ እና የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር መሐመድ አህመድ የተገኙ ሲሆን ከሠልጣኞች ለተነሱ ጥያቄዎችና ወደፊት የሚጠበቁ አቅጣጫዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ አቶ መሐመድ፣ ኢንስቲትዩቱ እንደሀገር በአመት 10,000 ባለሙያዎች ያሰለጥናል ከነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ደግሞ የፊልድ ኤፒዲሞሎጂ ሰልጠኞች ሲሆኑ ስልጠናው ከ43ቱ ማዕከሉ ዕውቅና ካገኘባቸው Continious Professional Development (CPD) ስልጠናዎች መካከል አንዱ እና ዋናው ነው::
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ጤና ቢሮ ተወካይ በበኩላቸው ስልጠናውን የወሰዱ ባለሙያዎች ወደ መጡበት ቦታ ሲሄዱ ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች የማካፈል እና የተማሩትን ወደ ተግባር የማውረድ ሀላፊነት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ ስልጠና ተግባራዊነት የበኩላቸውን የተወጡትን የኢትዮጰያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትንና US CDCን አመስግነዋል::
ወ/ሮ ነኢማ በበኩላቸው ስልጠናውን በትጋት ተከታትለው ለምርቃት የበቁትን አመሰግነው የሕብረተሰብ ጤና አዳጋዎች ቁጥጥር ባለሙያዎችን አስመልክቶ ያለውን የስራ ድልድል ሁኔታ ቀስ በቀስ የሚሻሻል መሆኑንና ስልጠናው ላይ ኮታ አስይዘው ስለጠናውን ሳይጨርሱ አቋርጠው ላቆሙት ከሚመለከታቸው የክልል ኃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩ አስረግጠው ተናግረዋል።