የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ ግምገማ እያካሄደ ነው

የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ ግምገማ እያካሄደ ነው
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ የኢንስቲትዩቱ ኃላፊዎች፣ የክልል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማዕከላት እና የላቦራቶሪ ኃላፊዎች እንዲሁም አጠቃላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከህዳር 1 እስከ 3/ 2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አጠቃላይ ግምገማ እያካሄደ ነው፡፡
የመድረኩ ዋና ዓላማ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የተሰሩ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን በመገምገም የተገኙ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል ክፍተቶችን ደግሞ ለማስተካከል የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንዲሁም የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የተለያዩ ሰነዶችን ማጽደቅ፣ ማስተዋወቅ እና ወደ ክልሎች ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የመክፈቻ ንግግር በአደረጉበት ወቅት እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ የሰጠውን ኃላፊነቶች በዝርዝር ከመጥቀሳቸውም በላይ ተቋሙ ወቅቱ የሚጠይቃቸውን የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከላትን ልዩ ትኩረት በመስጠት የማጠናከርና ለሚከሰቱ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የጤና አደጋ ወረርሽኞች ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያስችል ደረጃ ማደራጀት መቻሉን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከጤና ሚኒስቴርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከ2 ዓመት በላይ የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራዎችን በመስራት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሃገሪቱ ከገባችው (IHR 2005) ስምምነት መሠረት ከጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ከ2011ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል (Public Health Emergency Operations Center) የተቋቋሙትን መረጃና ሃብትን በማስተባበር የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን በፍጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት እንዲኖር እየተደረገ ይገኛል ሲሉ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ከፍተኛ ፈተናዎችን ፈጥሮ እንደነበረና ወረርሽኙን ለመቋቋም በነበረው የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች በጤናው ዘርፍ የላቦራቶሪ እና መሰል አቅም ግንባታ ላይ እንዲሁም በጋራና በቅንጅት የመስራት ባህልን በማዳበሩ በኩል መልካም የሆኑ አጋጣሚ መፈጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ እስከ አሁን የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ የዳሰሳ ጥናት በመድረኩ ቀርቦ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችና ክፍተቶች ተገምግመው የቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ እንዲሁም የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባባሪ ማዕከል ውጤታማ የተሻሉ ስራዎችን ለማሰራት ይችል ዘንድ በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀውን መመሪያ እና የስልጠና ማነዋል የማጸደቅና ለተጠቃሚ ተደራሽ የሚደረግ ተግባራት በመድረኩ የሚከናወኑ መሆናቸውን አቶ ሻምበል ሀቤቤ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል ም/ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡