የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓትን በጤና ተቋማት ላይ ያለውን የትግበራ ሁኔታ አስመልክቶ ግምገማ ተካሄደ
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል ከResolve To Save Lives (RTSL) ጋር በመተባበር የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓትን በጤና ተቋማት ላይ ያለውን ትግበራን አስመልክቶ ከሕዳር 19 እስከ 20/2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የግምገማ መድረክ አካሄደ፡፡
የመድረኩ ዋና ዓላማ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓትን ማለትም የቅድመ ዝግጁነት፣ መለየት፣ ምላሽ መስጠትና መልሶ ማቋቋም ስራዎችን በጤና ተቋማት ላይ ያለውን የትግበራ ሁኔታ ምን እንደሚመስል በመገምገም፣ጠንካራና እና ተግዳሮቶችን በመለየት የሚጠናክርበትን ሁኔታ ውይይት ለማድረግ ነው፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ ዋና ዳይሬክተር በግምገማ መድረኩ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት በጤና ተቋማት ላይ ተግባራዊ የተደረጉት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን፣ በቀጣይም በጤና ተቋማት ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ፣ አሁንም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን፣ የባለሙያዎችን አቅም ከመገንባት አንጻርም በክልል ጤና ተቋማት በርካታ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ የጋራ እቅዶችን በማውጣት ጠንካራ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ፣ ለአተገባበሩም አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ ተገቢ መሆኑን፣ የሚታዩ ክፍተቶችን ቅኝት በማድረግ የመለየት፣ መፍትሔ የማስቀመጥ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና ኢንስቲትዩቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው በጤና ተቋማት የተተገበሩ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ከማስቻላቸውም በላይ በመድረኩ በተካሄደው ግምገማ ለቀጣይ ስራዎች አቅጣጫዎች መቀመጣቸው አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፤ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስራዎችን በጤና ተቋማት መተግበር የሚገባቸውን ተግባራት በሚገባ በመለየት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ በጤና ተቋማት ያለውን ትግበራ አስመልክቶ በኢንስቲትዩቱ በ102 ሆስፒታሎች ላይ የተሰሩ ስራዎችን የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና በቀጣይ መደረግ የሚገባቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ወ/ሮ ምርትነሽ ሰልፉ የኢንስቲትዩቱ የመሰረታዊ ጤና አገልግሎት ዝግጁነትና ቀጣይነት ዲቪዥን አስተባባሪ አቅርበዋል፡፡ ከአጋር ድርጅቶች ደግሞ RTSL በ አዲስ አበባ አና በሲዳማ ክልል በ52 ጤና ጣቢያዎች ተግባራዊ መደረጉን እንዲሁም የትመረጡ ሆስፒታሎችና የክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች አተገባበሩን አስመልክቶ በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ የቀረቡ ሃሳቦችን መሰረት በማድረግ ሰፊ ውይይት እና ግምገማ የተደረገ ሲሆን በዚህም ይህንን በሚተገብሩ ተቋማት ላይ የበሽታ ቅኝት፣ ዝግጁነት፣ ምላሽ የመስጠትና መልሶ ማቋቋም ትግበራ መጠናከሩ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ ክልሎች መሰራት የሚገባቸውን ለይተው የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማዉጣት ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ስራ ሁሉ ከሚመለከታቸው የጤና ተቋማት እና ክኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት ጋር በመተባበር እንድሚሰሩ ከመድረኩ ውይይትና ግምገማ መረዳት ተችሏል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የኢንስቲትዩቱ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የክልል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር እና የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የተመረጡ ሆስፒታሎች እንደሁም የአጋር ድርጅት ተወካዮች በመድረኩ ተሳትፈዋል፡፡