የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረም ተጀመረ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2014 በጀት ዓመት ሁለተኛው የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረም በዛሬው ዕለት በሐረር ከተማ በደማቅ ሁኔታ የተጀመረ ሲሆን እስከ መጋቢት 17/2014 ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የሐረር ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ኢብሳ ሙሳ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ስለፎረሙ ዓላማ ካብራሩ በኋላ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስተር ዲኤታ የተከበሩ ወ/ሮ ሰሀርላ አብዱላሂ ፎረሙ በይፋ መጀመሩን አብስረዋል፡፡
ዶ/ር ኢብሳ እንደጠቀሱት በዚህ ማሕበረሰቡ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ ባለበት ወቅት የህንን ፎረም ለማዘጋጀት ክልሉ እድል በማግኘቱ ኩራት እንደሚሰማቸው እና በክልሉ የተቋቋመው የህብረተሰብ ጤና ደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያም እንዚህን ችግሮች ለመከላከል በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ጠቅሰው በፎረሙ የሚቀመጡ ቀጣይ አቅጣጫወችም ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ግልጸዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ መድረኩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥርን በሁሉም መዋቅሮች ለማሳለጥ የሚረዳ መሆኑን እና ከዚህ በፊት የሰራናቸውን ስራዎች የምንገመግምበት፣ ያጋጠሙን ችግሮችን የምንፈትሽበት፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችን የምናስቀምጥበት፣ ባለፈው ጉባዔ ላይ ያስቀመጥናቸውን አቅጣጫዎች ምን ላይ እንደደረሱ፣ አዲስ የተከሰቱ እና በድጋሚ የተከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ላይ ተወያይተን ቀጣይ መፍትሔዎችን የምናፈላልግበት የውይይት መድረክ እንደመሆኑ መልካም አፈጻጸማችንንም የምንለዋወጥበትም ጭምር ነው፡፡ ይህም ደግሞ ኮቪድ-19ን እና ሌሎች ወረርሽኞችን እንዴት በተሳካ ሁኔታ ምላሽ እንደተሰጠ እና በነበሩ የክትባት ቅስቀሳ ዘመቻዎች የነበሩ ልምዶችን የሚቃኝ ሲሆን በተጨማሪም በጦርነት፣ በሀገሪቱ በተከሰው ድርቅ እና በሌሎች ክስተቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የተሰጡ የተለያዩ ጤና ነክ ምላሾችን የምንገመግምበት እና ቀጣይ ልምዶችን የምንቀምርበት መድረክ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስተር ዲኤታ የተከበሩ ወ/ሮ ሰሀርላ አብዱላሂ በመክፈቻ ንግግራቸው
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ሚኒስቴር የቴክኒካል ክንድ በመሆን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በተቀመጠለት መስፈርት ምላሽ ለመስጠት የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርአትን በመገንባት፣የተጠናከረ የቅኝት እና ምላሽ እንዲሁም መልሶ የማቋቋም ተግባራቶችን በመተግበር የማይበገር የጤና ስርዓትን ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ስራዎችን ለማሳለጥ ያስችል ዘንድ መደበኛ በሆነ መልኩ የሕብረተሰብ ጤና ጉባኤ በየሩብ አመቱ በዋና ዋና የህብረተሰብ ጤና አጀንዳዎች ላይ ከጤና ሚኒሰቴር፣ ከክልሎች እና ገዳዩ ከሚመለከታቸዉ ባልድርሻ አካላት በትብብር በመወያየት የመፍትሄ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ክትትል እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
“ከዚህም ባሸገር በክልል ደረጃ የሚገኙ የማስተባበሪያ ማእከላትን በማስፋፋት ወደ ዞን እና ወረዳ ደረጃ በማስፋፋት ላይ የገኛል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ በሁሉም ክልሎች እና በተመረጡ ወረዳዎች የነጻ የስልክ ጥሪ ማእከል እንዲኖራቸዉ በማስቻል የኮቪድ እና የሌሎች የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ጭምጭምታ በመለየት መደበኛ የሆነዉን የበሽታዎች አሰሳ እና ቅኝት ከመንግዜዉም በበለጠ መልኩ እንዲጠናከር ማድረግ ተችሏል፡፡ ሆኖም ግን ሌሎች የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች አሰሳ፣ቅኝት እንዲሁም ምላሽ ከምንጊዜም በተሸለ መልኩ በተቀመጠለት የልኬት መስፈርት አመርቂ ዉጤት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ለኮሌራ ወረርሽኝ በተሰራው ዘርፈ ብዙ ስራ የኮሌራ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ተችሏል፣” ብለው ካብራሩ በኋላ ፎረሙ በይፋ መጀመሩን አብስረዋል፡፡
እንደሚታወቀው ይህ ፎረም ባለፈው ሃዋሳ ከዛ በፊት ደግሞ በድሬዳዋ መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡