የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝት መረጃዎችን ለማዘመን የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ

የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝት መረጃዎችን በዲጂታል ሥርዓት ለማዘመን የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) በሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ስር በሚገኘው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና በሽታ ኢንተለጀንስ ዲቪዥን ከኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር ከግንቦት 10 እስከ 14/2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የወረርሽኝና የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጠ።

የስልጠናው ዋና ዓላማ በሁሉም የጤና ተቋማት ውስጥ ወቅታዊ፣ ምሉዕ እና ጥራቱን የጠበቀ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃን በዲጂታል መንገድ ማሰባሰብ፣ ማደራጀትና መተንተን የሚያስችል አቅም መገንባት ነው። ይህም ውሳኔ ሰጪ አካላት ፈጣንና ውጤታማ የወረርሽኝ መከላከልና ምላሽ ሥራዎችን ለመስጠት የሚያስችላቸውን መረጃ በወቅቱ እንዲያገኙ ያደርጋል።
አቶ ማንደፍሮ ከበደ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና በሽታ ኢንተለጀንስ ዲቪዥን ኃላፊ በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንደገለጹት፤ ሀገሪቱ የምትከተለውን የወረርሽኝ መረጃ ልውውጥ ሥርዓት ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የዲጂታላይዜሽን ሥራው ወሳኝ መሆኑን፣ ለዚህም በዘርፉ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በተለያዩ ዙሮች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ማንደፍሮ አክለውም፣ ሰልጣኞቹ በመረጃ አሰባሰብ፣ በጥራት ቁጥጥር፣ በትንተና፣ በሪፖርት አቀራረብ፣ በግብረ-መልስ አሰጣጥ እና ለውሳኔ ሰጪዎች ሪፖርት በማድረግ ረገድ ሰፊ እውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ለቀጣዩ የComprehensive PHEM DHIS2 ሥርዓት ሙሉ ትግበራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
አቶ መሐመድ አህመድ የኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር በስልጠናው ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ስልጠና ማዕከል በርካታ መደበኛና ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ (CPD) ስልጠናዎችን በመስጠት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመው፣ መረጃን ከማዘምን ጋር ተያይዞ ወቅቱ የዲጂታላይዜሽን ሽግግር ላይ በመሆኑ ተከታታይነት ያለው ሞጁል እስታንዳርድ የሆነ የዲጂታላይዝ የሙያ ብቃትን መሰረት ያደረገ ለጤና ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ ስልጠና መሆኑን እና በቀጣይ ስልጠናውን በተሻለ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ይህንን የዲጂታላይዜሽን ሽግግር ውጤታማ ለማድረግ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና ከፕሮጀክት ሆፕ (Project HOPE) ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል። ኢንስቲትዩቱ ለሥርዓቱ ማስፈጸሚያ የሚሆኑ በርካታ ኮምፒውተሮችንና የኤሌክትሮኒክስ ግብዓቶችን ለጤና ተቋማት ያሰራጨ ሲሆን፣ ስልጠናውም ከድርጅቶቹ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ከመድረኩ መረዳት ተችሏል።
በስልጠና ፕሮግራሙ ላይ የሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ጤና መምሪያ ጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ሰልጣኞች ስልጠናውን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቁ በመሆናቸው የእውቅና ሰርተፍኬት የተቀበሉ ሲሆን፣ በቀጣይም ወደ የመጡበት ተቋም በመመለስ ያገኙትን ስልጠናውን እውቀትና እና ክህሎት ስልጠናውን ላላገኙ ሌሎች የጤና ባለሙያዎች በተዋረድ (Cascade) የመስጠትና ሥርዓቱን በየደረጃው የማስፈጸም ኃላፊነት ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡