የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሥራ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት የስድስት ወር አፈጻጸም ግምገማ አካሄደ
January 12, 2021
በኢትዮዽያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሥራ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት በቢሾፍቱ ከተማ የስድስት ወር አፈጻጸም ግምገማ አካሄደ፡፡ በግምገማው ላይ በቀጥታ ስራው ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በተለያየ መንገድ ለእቅዱ መሳካት ድጋፍ የሚያደርጉ ዳይሬክቶሬቶችም ተገኝተዋል፡፡ ግምገማውን የመሩት የኢትዮዽያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የግምገማውን ዓላማ ሲገልጹ የሪሰርችና ቴክኖሎጂ ትራንስፈር ዘርፍ ከምንጊዜውም በላይ ተናቦ በመንቀሳቀስና ከሌሎች የሥራ ክፍሎች ጋር ጤናማ የሥራ ግንኙነት በመፍጠር ለኢንስቲትዩቱ ራዕይ መሳካት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ለማድረግ እንዲቻል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እያንዳንዱ ዳይሬክቶሬትም የስድስት ወር አፈጻጸሙን ካቀረበ በኃላ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው የተስተናገዱ ሲሆን ጠንካራ የሆኑ ጎኖቹ ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በሌላም በኩል ደግሞ የታዩ ደካማ ጎኖችን በቀሪው ግማሽ ዓመት በማስተካከል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል በዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ አቅጣጫ ተሰጥቶበት የአንድ ቀን መርሀ ግብሩ ተጠናቋል፡፡