የምርምር ሥራዎች ውጤታማ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ሳይንሳዊ መርህን የተከተሉ የፕሮፖዛል አፃፃፍ እና አዘገጃጀት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚያዚያ 16/2015 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲያኪያሂድ በነበረው የምርምር ሥራዎችን ለማካሄድ የሚረዳ ገንዘብ (ግራንት) ለማግኘት የሚያስችል አፃፃፍ እና አዘገጃጀትን በተመለከተ የተዘጋጀው ወርክሾፕ አስተባባሪ የሆኑት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ሥነ-ምግብ ምርምር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር አረጋሽ ሳሙኤል እንደገለጹት ሥልጠናው የተሳታፊዎችን የምርምር ክህሎት እና ግንዛቤ ለማዳበር እንዲሁም ልዩ ልዩ ፕሮፖዛሎችን በማዘጋጀት ወደ ሀገር ውስጥ ገንዘብ ማምጣት የሚቻልበትን ስልትና ክህሎትን ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ተቋማዊ ትስስርን ለመፍጠር እና በምርምር ዙሪያ ያሉ የሥነ-ምግባር መርሆዎችን ለማስጨበጥ እንዲቻል ወርክሾፑ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ዶ/ር አረጋሽ አያይዘው ገልጸዋል።
አቶ መሐመድ አሕመድ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የሥልጠና ማእከል ዳይሬክተር በበኩላቸው የሥልጠና ማእከሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ልዩ ልዩ ስልጠናዎችንና የአቅም ማጎልበቻዎችን በማዘጋጀት የባለሙያዎችን አቅምን በማሳደግ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ አብራርተዋል።
አቶ መሐመድ አያይዘውም የስልጠና ማእከሉ ቀደም ሲልም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመራማሪዎችን እና የተቋማትን አቅም ለማጎልበት እንዲቻል ልምድ ያላቸው አሰልጣኞችን በማስመጣት የተለያዩ ሥልጠናዎችን የሰጠ ሲሆን በቀጣይነትም መሰል ስልጠናዎችን ለልዩ ልዩ ተቋማት እንደሚያዘጋጅ አስረድተዋል።
በስልጠናው ላይ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ከሲዳማ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የተውጣጡ 28 በጤና እና በሥነ-ምግብ ሥራ ዙሪያ ላይ የተሰማሩ ተመራማሪዎች ተካፋይ ሆነዋል።