የምስጋና ቀን ተከበረ::
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የማናጅመንት አባላትና ሠራተኞች በዛሬው ዕለት የምስጋና ቀንን በኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ ውስጥ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አከበሩ፡፡ በእለቱ “ኢትዮጵያ ታመስግን” በሚል መሪ ቃል በተከናወነው ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር እንዳስገነዘቡት ሀገራችን ኢትዮጵያ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ በአሸናፊነት በማለፍ አሁን ላለችበት ቁመና መድረሷን አውስተው ለእዚህም ፈጣሪያችንን ልናመሰግን ይገባል ብለዋል፡፡ ትናንት አባቶቻችንና እናቶቻችን እስከ ህይወት መስዋትነት ድረስ የሚከፈለውን ሁሉ በመክፈል ሀገራችን ለእኛ በማስረከባቸው ልናመሰግናቸው የሚገባ ሲሆን አሁን ደግሞ በመላው ሀገራችን በልዩ ልዩ የስራ ዘርፎች በመሰማራት ሀገርና ህዝባቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በታማኝነትና በቅንነት ለሚያገለግሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልናመሰግናቸው ብሎም ልናከብራቸው ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በቅርቡም ሀገራችንን በዓለም አትሌቲክስ አደባባይ በተደጋጋሚ ከፍ ብላ እንድትታይ እና ስሟ በአድናቆት እንዲጠራ ያደረጉት አትሌቶቻችን ያስተማሩን ነገር ቢኖር በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን እና ተባብረን እንዲሁም ተሳስበን በህብረት ከሰራን ዓለምን ማስደመም ብሎም ካሰብንበት የከፍታ ማማ ለመውጣት ምንም ነገር የሚያግደን ነገር እንደማይኖር አመላክቶናል ብለዋል፡፡
እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ ዛሬም እንደ ትናንቱ በርካታ ፈተናዎችን በድል በመሻገራቸው የተነሳ ዛሬም እጃችንን ለምስጋና መዘርጋት እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡ አመስጋኝነት ያለፈውን ዘመን በአሸናፊነት፤ ያለንበትን ወቅት ደግሞ በዕድለኝነት፤ መጪውን ጊዜ ደግሞ በብሩህ ተስፋ እንድንመለከተው የሚያደርግ ታላቅ ሀይል እንዳለው አስረድተዋል፡፡
በዕለቱ በተከናወነው መርሀ ግብር መሰረት የኢንስቲትዩት የማናጅመንት አባላትና ሠራተኞች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ያላቸውን ክብር የገለጹ ሲሆን ለታላቂቷና ለጥንታዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ ያላቸውን የልጅነት ፍቅር በጭብጨባና በእልልታ ገልጸዋል፡፡ በዚሁ የምስጋና ቀን መርሀ ግብር ላይ ልዩ ልዩ ሀገራዊ ጣዕመ ዜማዎች የቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተዘምሮ የፕሮግራሙ ፍጻሜ ሆኗል፡፡