የምግብ ዘይቶችን በተለይም በፓልም ዘይት ዙሪያ በተደረገው የጥናት ውጤት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሃገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ዘይቶች ላይ ያደረገውን የምርምር ጥናት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ ለተለያዩ የሚዲያ አካላት ሰኔ 5/2011 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማእከል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ያስፈለገበት ምክንያት በተለያዩ ሚዲያዎች እና የህብረተሰብ አካላት የምግብ ዘይቶች ላይ ለሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችን መልስ ለመስጠትና ስለምግብ ዘይት የተሰራ ጥናት አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የምግብ ዘይቶችን እስመልክቶ እንደገለጹት በምግብ ዘይቶች ላይ ከህብረተሰቡና ከተለያዩ አካላት የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ በጤና ሚኒስቴር በምግብ ዘይቶች ላይ ጥናት እንዲደረግ አቅጣጫ በማስቀመጡ ኢንስቲትዩቱ 7 በሃገር ውስጥ በሚመረቱትና 9 ከሃገር ውጪ በሚገቡ በአጠቃላይ በ16 የምግብ ዘይት አይነቶች ላይ ጥናት ያደረገ ሲሆን ጥናቱም መሰረት ያደረገው ከጥራትና ከጤና አንጻር መሆኑን እና ህብረተሰቡ ላይ ሊያመጡ የሚችሉትን የተለያዩ አሉታዊ ተጽእኖዎች በመፈተሽ ለሚመለከተው አካል የጥናቱ ሪፖርት መቅረቡን ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫው ተናግረዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ጥናቱን ሲያጠና የአለም ጤና ድርጅት ካወጣው እስታንዳርድ ላይ በመመሰረት የላቡራቶሪ እንሰሳትን ተጠቅሞ የምግብ ዘይቶቹን የገመገመና የፈተሸ ሲሆን በሃገር ውስጥ የሚመረቱት ፈሳሽ ዘይቶች የአመራረት የጥራት ደረጃ ችግር ያለባቸው መሆኑንና በጤና ለይ ግን ችግር የማያስከትሉ መሆናቸውን ጥናቱ መረጋገጥ መቻሉን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
ከውጪ የሚገቡት በተመለከተ በተለይ የሚረጋው ዘይት ከፍተኛ የሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ መጠን ያለው ሲሆን ይህም በተደጋጋሚ መጠቀምና ለረጅም ጊዜ መጠቀም ለኮሊስትሮል የሚያጋልጥ በመሆኑ አመጋገብ ላይ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ እና ሁልግዜ መጠቀም ለጤና ችግር እንደሚያጋልጥ ዋና ዳሬክተሩ አያይዘው ሰፊ ማብራሪያ ሰጠዋል፡፡
የምግብ ዘይቶችን አስመልክቶ የንግድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቲር የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ በመሆኑ በቀጣይ ጥናቱን መሰረት በማድረግ በቅርብ ቀን የተለያዩ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ እንጠብቃለን እንዲሁም ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ የሚረጋ ዘይትን በብዛት የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጤና አስመልክቶ ጥናት ለማድረግ የንድፍ ዝግጅቱንም አጠናቀዋል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡