የሠራተኛ ማህበራዊ ሻይ ክበባት በምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ውጤታማ ከሚያደርጋቸው በርካታ ጉዳዮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ተቋማቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በተማረ የሰው ኃይል ማደራጀት እና ለተቋሙ አገልግሎት ለሚሰጡ ሠራተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታን መፍጠር መሆኑ አያጠያያቂ ባይሆንም ለሰራተኞች ልዩ ልዩ ግልጋሎት የሚሰጡ ክበባት በበኩላቸው የሚያደርጉት አስተዋጸኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም የሠራተኞቹን የስራ ተነሳሽነት፤ ስሜትና ፍላጉት ከመጠበቅ አንጻር ካደረጋቸው በርካታ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የሠራተኛ ማህበራዊ ሻይ ክበብ ማቋቋምና ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጥ ማድረግ ሲሆን ማሕበራዊ ሻይ ቤቱ ህዳር 9/2016 ዓ.ም እለት 49ኛ ዓመት ዓመታዊ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ አከብሯል፡፡
የእለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር እና የክበቡ የበላይ ጠባቂ የሠራተኛው ማህበራዊ ሻይ ክበብ ለጠቅላላ ሰራተኞች ግልጋሎት እንዲሰጡ ያስገነባቸውን የሱፐር ማርኬት ማዕከል፣ የወፍጮ ቤት፤ የማህበራዊ ሻይ ቤት የማስፋፊያ ስራዎች ማለትም የጤፍ፣ የሽሮና የበርበሬ፣ የቆሎ መፈተጊያ ወፍጮዎች፣ የስጋ ማቀነባበሪያና የሥጋ ቤት፤ የእንጀራ ቤት ከመረቁ በኃላ ባደረጉት ንግግር ማሕበራዊ ሻይ ቤቱ የሠራተኞችን መሰረታዊ ጥያቄዎችን በማሟላቱ ረገድ ያደረገው እንቅስቃሴ አስመስጋኝና የሚያበረታታ ለሌሌችም ተቋማት አርአያ ያለው በመሆኑ ኢንስቲትዩቱ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ አሁንም ቢሆን ድጋፍና እገዛውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ማሕበራዊ ሻይ ቤቱን በተለያዩ መንገድ ድጋፍና አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩ ባለሙያዎችና አካላት የእውቅና ሰርተፍኬት የሽልማት ስጦታ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን የዛሬ ግማሽ ምዕተዓመት በ1967 ዓ.ም ከሠራተኞች አንድ፤ አንድ ብር መዋጮ በማዋጣት ለምሳ ንፍሮና ሻይ በማቅረብ የተቋቋመውና በአሁኑ ወቅት በየቀኑ ከ1200 በላይ ሠራተኞች ልዩ ልዩ የምግብ አገልግሎት በየቀኑ መስጠት ላይ የሚገኘው ማሕበራዊ ሻይ ቤቱ በቀጣይ ተጨማሪ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ የግንባታና የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤናው ዘርፍ የምርምር ተቋም እንደመሆኑ መጠን በተለይም የምግብ ደህንነት ሥርዓትን ለማረጋገጥ እንዲቻል በሙያው በተመረቁ ባለሙያዎች በመቅጠር ክበቡን የሚያንቀሳቅስ ሲሆን የኢንስቲትዩቱን ተመራማሪዎችና የተለያዩ ባለሙያዎች በማሳተፍ የካበተ የዕውቀትና የልምድ ምክር ሃሳብ በመጠቀም የበለጠ ዘላቂና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የማቻልበትን መንገዶች በመቀየስ ላይ ይገኛል፡፡ ክበቡ በርካታ ሀገራዊ ግዴታዎችንና ኃላፊነቶችን በየጊዜው የተወጣ ሲሆን ለአብነት ያህልም በዓለም ላይ የጤና ቀውስ በተፈጠረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተነሳበት ወቅት ኢንስቲትዩቱ ይህንን ወረርሽኝ ለመቆጣጠርና ለመከላከል በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለተሠማሩ ባለሙያዎች በየቀኑ እስከ ሶስት ሺህ የሚደርሱ የታሸጉ ምግቦችን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የምግብ አገልግሎት በማቅረብ ታላቅ ሀገራዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡