የሬዚለየንስ የጤና ስርዓት መገንባት ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የመልሶ ማቋቋም እና የሬዚለየንስ ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከዓለም የጤና ድርጅት፣ከቫይታል ስትራቴጅስ ኢትዮጵያ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን መቋቋም የሚችል የጤና ስርዓት ለመገንባት የአሰልጣኞች ስልጠና በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ይገኛል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስተር ዲኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በመክፈቻ ንግግራቸው ይህ ወሳኝ የሆነ የአሰልጣኞች ስልጠና ማንዋል እንዲዘጋጅ ያስተባበሩትን እና የተሳተፉትን በሙሉ አመስግነው፣ ሬዚለንየስ የጤናሥርዓት መገንበት በዚህ ዓመት በተከለሰዉ የጤና ፖሊስ የትኩረት አቅጣጫዎችዉስጥ አንዱ ሲሆን ይህም ላለፉት 25 ዓመታት ሲተገበሩ በነበሩት የጤና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ዉሰጥ በበቂ ሁኔታ ያልተካተተ ነበር።
ይህ ስልጠና የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን መቋቋም የሚችል የጤና ስርዓት በመገንባት ስጋቶችን ቀድሞ መለየት፤መከላከል እና ቢከሰቱም ምን መደረግ እንዳለበት ተገቢዉን ዝግጅት ማድረግ እና ከዚህም ባለፈ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን የማስቀጠል አቅምና ልምምድን መፍጠርላይ ያተኩራል። ብዙ ጊዜ አደጋ ሲፈጠር ብቻ ነው ምላሽ ለመስጠት የምንሯሯጠው፣ ይህ ደግሞ በኢኮኖሚም ሆነ በሰው ሀይል ከፍተኛ ብክነት ያስከትላል። ይህን ለማስቀረት ስልጠናዉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል በማለት ዶ/ር ደረጀ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው መጀመሪያ ላይ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የመልሶ ማቋቋም እና የሬዚለየንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ያረጋል ፉፋ እንደገለጹት ወደ ስድስት የሚደርሱ ሀገር ዓቀፍ የዳሰሳ ጥናቶችዉጤት ላይ በመመስረት ሶስት በሀገር ደረጃ የሚተገበሩ ሰነዶች (የሬዚለንስ የጤና ስርዓት ኢኒሸቲቭ፣የሬዚለንስ የጤና ስርዓት ማዕቀፍ እና የሬዚለንስ የጤና ስርዓት የስልጠና ማኑዋል) ለማዘጋጀት ችለናል። ይህ ስልጠና ማኑዋል ከ30-40 ሰዓት የሚወስድ ሲሆን በዓለም የጤና ድርጅት፣በአዲስ አበባ እና በኢዲንቡርግ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ የተዘጋጀ ነዉ።
ዶ/ር ያረጋል ስለ ስልጠናው ሲያስረዱ ስልጠናው አራት ሞጁውሎች ያሉት ሲሆን እነሱም፣ መሰረታዊ የሬሲልየንስ ጭብጦች፣ ቅድመ የጤና አደጋዎች መከላከል እና ዝግጁነት፣ በአደጋ ጊዜ የምላሽ አሰጣጥ እና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ማስቀጠል እና ከአደጋ በኋላ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ላይ የተኮረ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡