የሰንደቅ ዓላማ ቀን በከፍተኛ ድምቀት ተከበረ፡፡
October 11, 2021
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም የፌደራል ፓሊስ አባላት በተገኙበት በዛሬው እለት የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በኢንስቲትዩቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በልዩ ልዩ ሥነ-ሥርዓቶች አከበሩ፡፡
የእለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የዘንድሮውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ልዩ የሚያደርገው ህዝባችን በነቂስ ወጥቶ የመረጠበትን ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በድል አጠናቀን የመንግስት ምስረታችንን በተሳካ ሁኔታ ባከናወንበት ማግስት በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ ሊሰማን ይገባል ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የሰንደቅ ዓላማ ማንነትን የተመለከተ ገለጻ የተደረገ ሲሆን ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር መታወቂያ፤ የሕዝብ አንድነት መጠበቂያ እንዲሁም የክብር መለያ ምልክት መሆኑ የተብራራና ሰንደቅ ዓላማ የአንድ መንግሥትና ሕዝብ ሉዐላዊነት፣ ስልጣንና ነፃነት ምልክት ወይም ተምሳሌት ተደርጐ እንደሚወሰድ ተገልጻል፡፡ በታሪክ ድርሳ መዛግብት ላይ እንደተመዘገበው ሰንደቅ ዓላማችንን ለማስከበር አባት፤ አያት፤ ቅድመ አያቶቻችን ደምና አጥንታቸውን በመከስከስ ህይወታቸውን በመገበር ያደረጉት ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ተጋድሎ እና ታሪክ ተወስቷል።