የስብአዊ እርዳታ አገልግሎቶች በሚሰጡበት ጊዜ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ማካተት አለባቸው ተባለ
ማናቸውም የስብአዊ እርዳታ አገልግሎቶች በሚሰጡበት ጊዜ መሰረታዊ የሆኑ የሥነ-ጻታ እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ማካተት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡ዶ/ር መሰረት ዘላለም በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና የህጻናት ዳይሬክተር ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የነበረውን መሰረታዊ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች የአሰልጣኞች ስልጠና መዝጊያ ስነ-ስርአት ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር እንዳሳሰቡት በማናቸውም ጊዜ የስብአዊ እርዳታ አገልግሎቶች በሚሰጡበት ጊዜ መሰረታዊ የሆኑ የሥነ-ጻታ እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ እንዲዳረሱ ማድረግ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በትብብር እና በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ዶ/ር መሰረት አያይዘውም ይህን ስልጠና የተካፈሉ ባለሙያዎች በበኩላቸው ከስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ተሞክሮ በዞን፡ በወረዳ እና በክልሎች ለሚገኙ የሙያ አጋሮቻቸው በማካፈል የእውቀትና የክህሎት ሽግግር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ዳይሬክተርዋ አያይዘውም መሰረታዊ የሆኑ የሥነ-ጻታ እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች እንዲስፋፉና እና መሰል ስልጠናዎች በየክልሎቹ እንዲሰጡ አጋር ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ያደርጉ የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አቅርበው ከባህር ማዶ በመምጣት ስልጠናውን የሰጡትን ባለሙያዎችና ስልጠናውን ያመቻቹትን ተቋማትን በሚኒስቴር መስርያ ቤታቸው ስም አመስግነዋል፡፡
ስልጠናውን የተካፈሉት ሰልጣኞች በበኩላቸው ስልጠናው ወቅታዊ የሆነውን አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን እና መሰረታዊ የሆኑ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች ዙርያ ያሉትን እውነታዎችና ክፍተቶችን እንዲሁም በቀጣይ መደረግ ስላለበት መሰል ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸው ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው መዝጊያ ሥነ-ሥርአት ላይ ዶ/ር መሰረት ዘላለም በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና የህጻናት ዳይሬክተር እና ዶ/ር በየበሩ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሥነ-ህዝብ ፕሮግራምን (UNFPA) በመወከል ለሰልጣኞቹ የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡