የባህል መድሃኒት ጥናትና ምርምር ፍኖተ- ካርታ ይፋ ሆነ
የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የባህል መድሃኒት ጥናትና ምርምር ፍኖተ ካርታ የጤና ሚኒስትሩ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ማህበራት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መስከረም 19 /2012 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ ይፋ አደረገ፡፡
የፍኖተ-ካርታው ዋና አላማ ሃገር በቀል ዕዉቀትን በመሰነድና በመጠበቅ የተጠናከረ ጥናትና ምርምር ማከናወን፣የባህል መድሃኒት ባለሙያዎችን ማደራጀት፤ የባህል መድሃኒቶች በፋብሪካ እንዲመረቱ ማስቻል፤ ጠንካራ የምርምር -ዩኒቨርሲቲ እና የፋብሪካ ትስስር መፍጠር፤ የቤተሙከራዎችን አቅም ማሳደግ፣ ደረጃውን የጠበቀ የፍቱንነት፣ የደህንነትና የጥራት የፍተሻ አገልግሎት መስጠት እና ከጤና ሚኒስቴርና ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር በመተባበር ደረጃውን የጠበቀ የባህል ህክምና አገልግሎት በአገሪቱ እንዲሰጥ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡
ደ/ር ኤባ አባተ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በፍኖተ ካርታው መክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደገለጹት የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአገራችን በአማካይ ወደ 80 በመቶ ሚሆነው ህዝብ የባህል መድሃኒት ተጠቃሚ ቢሆንም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ግን ብዙም ይደለም፤ በመንግስት ደረጃም እውቅና ያገኘው በ1942 ዓ.ም ነው፡፡
ነገር ግን አሁን የጤና ሚኒስቴር የባህል መድሃኒትን ትልቅ ትኩረት ሰጥቶት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲያስተባበርና ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ በመደረጉ ፍኖተ ካርታው ተዘጋጅቶ በመጠናቀቁ ለዚህ መድረክ የቀረበ ሲሆን ጤና ሚኒስቴርም ለተግባራዊነቱ 90 ሚሊዮን ብር መድቧል ሲሉ ሰፊ ማብራሪያ ስጥተዋል፡፡
ዶ/ር አሚር አማን የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላት መልከዓ ምድር እና አየር ንብረት ከ6500 በላይ የሚሆኑ የመድሃኒት እጽዋት፣በርካታ እንሰሳት እና መዕድናት መገኛ መሆኗ፣ ከ 80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝቧ ሲታመም መጀመሪያ የሚጠቀመው የባህል መድሃኒት መሆኑ እና ረጅም ዓመት የተካበተ እውቀት ያለ ቢሆኑም መጠቀም ግን አልተቻለም በመሆኑም የሃገራችን ህዝብ ተፈላጊውን ጥቅም እንዲያገኝ ለማስቻል የባህል መድሃኒት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ትልቁ ጉዳይ በመሆኑ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ብለዋል፡፡
በቀጣይ በባህል መድሃኒቶች ላይ የተለያዩ ጥናትና ምርምር በጋራ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ ከሁሉም የሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና ከምርምር ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመ ሲሆን በፍኖተ ካርታው እና ባህል መድሃኒት ምርመር ላይ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ለፕሮፌሰር አርዓያ ሃይመተ እና ለፕሮፌሰር ኢያሱ መኮንን እንዲሁም ከኢንስቲትዩቱ ለዶ/ር አስፋው ደበላ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ሽልማቶች አበርክቶላቸዋል፡፡
በመደረኩ ላይ የጤና ሚኒስትሩ እና ሌሎች የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የፓርላማ አባላት ፣ የባህል መድሃኒት ማህበር ተወካዮች ፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን እስከ መስከረም 21/2012 ዓ.ም የተለያዩ ጥናቶች እየቀረቡ ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑ ከመድረኩ መረዳት ተችሏል፡፡