የባዮ ባንክና የላቦራቶሪ ጥራት ማረጋገጫ ናሙናዎች ማምረቻ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ተጣለ

በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚገነባው የባዮ ባንክና የላቦራቶሪ ጥራት ማረጋገጫ ናሙናዎች ማምረቻ (Bio-Bank and Proficiency Panels Production Center) እንዲሁም የሴንትራል ዌር ሀውስ (Central Warehouse) ህንጻ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ነሀሴ 7/2015 የጤና ሚንስቴር ሚንስትር፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲተዩት ዳይሬክተሮች እና የጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ሀላፊዎች በተገኙበት ተጣለ።
የጤና ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በስነ ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት የላቦራቶሪ አገልግሎት በዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርት ደረጃውን ጠብቆ መሰጠቱን እና የላቦራቶሪ መመርመሪያ መሳሪያዎች ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲሁም የላቦራቶሪ ባለሙያዎች በስታንዳርድ መሰረት ምርመራዎችን ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ የጥራት ፍተሻ ናሙናዎች አስፈላጊ እንደመሆናቸው ሀገራችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየተገዙ ለጥቂት ላቦራቶሪዎች ብቻ እያቀረበች ያለች ሲሆን ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ግን የጤና ተቋማት እነዚህን ናሙናዎች በሀገር ውስጥ ማግኘት ያስችላል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው በዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ውስጥ የባዮባንክ አገልግሎት አንዱ ሲሆን ይህም የተለያዩ በሽታ አምጪ ተህዋስያንን የያዙ ናሙናዎችንና ተያያዥ መረጃዎችን በከፍተኛ ጥንቃቄ መያዝ እና በባንክ ስርዓት ማስተዳደር ማስተዳደር የሚያስችል ስርዓት እነደሚገነባ ገልጸዋል።
ዶ/ር መሳይ አያይዘውም ይህ ስርአት በሽታዎች ላይ የሚደረጉ ማንኛውንም አይነት ጥናትና ምርምሮች ለማከናወን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ የላቦራቶሪ መመርመሪያ ኪቶችን ለማዘጋጀት እና ለጥራት ፍተሻ ናሙና ማምረቻ ማእከሉም እንደ ጥሬ እቃ ናሙናዎችን በማቅረብ የጥራት ፍተሻ ናሙና የማምረት ስራውን የሚያግዝ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ይህ ግንባታ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የሚከናወን ሲሆን ግንባታውም በሁለት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ እና ወደ 900 ሚሊዮን ብር የሚያስወጣ ሲሆን ግንባታውን ለማካሄድም ጨረታውን ካሸነፈው ሀገር በቀል ከሆነው ኔማር ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ጋር ውል ተፈርሟል።