የብሄራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር፤ ቅመራና ትንተና ማዕከል ሃላፊዎች ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ
በአገራችን የጤናና ጤና ነክ ዳታዎች ተሰብስበውና ተቀምረው ለሚፈለገው ጥቅም ለማዋል አዳጋች ሆኖ ነበር የቆየው፡፡አገሪቱ ያሉዋት ጤና ነክ ዳታዎች ሃብትና ብዛት፤በማን እጅ እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አመላካች የሆኑ ስራዎችም አልተሰሩም፡፡ይህም በመሆኑ በብዙ ልፋትና ድካም የተሰበሰቡ ዳታዎች እንዲሁም በርካታ ገንዘብ ፈሶባቸው የተሰሩ የምርምር ስራዎች ተበታትነው ይገኛሉ፡፡በዚህ የተዝረከዘረከ አሰራር ምክንያት አገራችን መሰረታዊ የሆኑ ጤናና ጤና ነክ ፖሊሲዎችን ለማውጣት የሚያስፈልጉዋትን መረጃዎችና ማስረጃዎች በአግባቡ ለማግኘት ተቸግራ ቆይታለች፡፡ይህ ችግር የተከሰተው የዳታ ማስረጃዎች ባለመኖራቸው ሳይሆን ያሉትን ዳታዎች በአግባቡ ባለመሰነዱ፤ሳይንሳዊ በሆነ ትንተናም ባለመዘጋጀቱ ነው፡፡ይህን መሰረታዊ ክፍተት በመገንዘብም የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት የብሄራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር፤ ቅመራና ትንተና ማዕከል አቋቁሟል፡፡
የዚህን ማዕከል ዓላማዎችና እያከናወናቸው የሚገኙትን ተግባራት አስመልክቶ ከማእከሉ አስተባባሪ ዶ/ር ዓለምነሽ ኃይለማርያ እና ከማዕከሉ አማካሪ ዶ/ር አወቀ ምስጋናው ጋር ቃለመጠይቅ አድርገናል፡፡
ጥያቄ- እስኪ ከአመሰራረቱ እንጀምር…አመሰራረቱ ምን ይመስል ነበር?
ዶ/ር ዓለምነሽ/ዶር/አወቀ -ማዕከሉን ለመመስረት የተለያዩ ጥረቶችና ቅድመ ዝግጅቶች የተጀመሩት ከአራት ዓመት በፊት ነው፡፡ዋናው መነሻ የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓት ስትራቴጂ ዶክመንቱ ላይ የተነሳው ችግር ነበር፤ይሄውም የዳታ አያያዝና አጠቃቀም ችግር በተለይም የዳታ ጥራትና ተደራሽነት ችግር መኖሩ ተጠቅሶ ነበር፡፡ዳታዎች ለፖሊሲና ፕሮግራም ቀረፃ ውሳኔዎች በሚያግዝ መልኩ ተተንትነውና ተቀናብረው አይቀርቡም ስለሆነም የመረጃ አብዮት ያስፈልጋል የሚል አቅጣጫ ተያዘ፡፡አገራዊ ተጨባጩን ስንመለከት የጤናው ዘርፍ የሚፈልገውን ዳታ በዘርፉ ለሚወጡ ፖሊሲዎች ግብዓትነት ተንትኖና ቀምሮ የማቅረቡ ልምድ አልነበረም፡፡ዳታዎች ጥራትና ወቅቱን በጠበቀ መንገድ አይሰበሰቡም፤አይቀመጡም፡፡ ኢንስቲትዩቱ በዚህ ረገድ ራሱን ሲፈትሽ በዳታ አያያዝና አስተዳደር ላይ ትልቅ ድክመት እንደነበረበት ታይቷል፡፡ኢንስቲትዩቱ ራሱ ያሰራውን ጥናት ለምኖ ነው ዳታ የሚቀበለው፡፡ ኢንስቲትዩቱ የጤና ሚኒስቴር የምርምርና ጥናት ክንፍ ቢሆንም ከተቋሙ የሚፈለገውን የዳታ ትንተናና ቅመራ ማቅረብና ለፖሊሲ ግብዓት መጠቀም የሚያስችል አቅም አልፈጠረም ነበር፡ በመሆኑም የጤና ነክ ዳታዎች የመረጃ ቋት ለማቋቋም ነው ይህ ማዕከል የተመሰረተው፡፡
ጥያቄ- ማዕከሉን ለመመስረት ዋና ዋና ምክንያቶች ምን ነበሩ?
ዶ/ር ዓለምነሽ-ለማእከሉ መመስረት በርካታ ገፊ ምክንያቶች ነበሩ፤በተለያዩ አካላት የሚሰበሰቡ ዳታዎች ወደ አንድ ቋት መጥተው ለሚፈለገው ጥቅም የሚውሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡አገራችን ላለፉት ሃያና ሃምሳ ዓመታት ምን ያህል የጤና ዳታ ሃብት እንዳላት አይታወቅም፤እነዚህ ሃብቶች የት እንዳሉ፤በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉም አይታወቅም፤የዳታ ሃብት አያያዝ፤ አጠቃቀም፤ዳታዎቹ ለሚፈለገው ጥቅም እንዲውሉ የተማከለ የትንተናና ቅመራ አሰራርም የለም፤የዳታ ፍሰትና ልውውጥን በተመለከተም የማስተዳደሪያ ስርዓትም አልነበረም፡፡ኢንስቲትዩታችን የጤና ሚኒስቴር የጥናት ክንፍ ቢሆንም ጤና ነክ የሆኑ አገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሲወጡ ደጋፊ የሆኑ ጥናታዊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ግብዓት የመስጠት ጥረቶች ብዙም አመርቂ አልነበሩም፡፡አንድ ጥናት ተሰርቶ ካለቀ በሁዋላ በቴክኒካል ሪፖርትና በተወሰኑ ህትመቶች ላይ የተገደበ ነበር ልምዱ፤ ስለዚህ ሳይንሳዊ ዘዴን ተጠቅሞ የላቀ የቅመራ ቴክሎጂን መሰረት አድርጎ መረጃ ማምረት ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ዓላማ አድርጎ ነው ማዕከሉ የተቋቋመው፡፡
ጥ-ማዕከሉ ምን አይነት ስራዎችን ለመስራት እንደተቋቋመ ትንሽ ዘርዘር አድርገው ቢያብራሩልን?
ማዕከሉ የተቋቋመው በሀገሪቱ እስካሁን የተሰሩትን እና ወደፊትም የሚሰሩትን የጤናና ጤና ነክ ጥናትና ምርምር፤የጤና አገልግሎት፤እንዲሁም የቅኝትና ሌሎች የጤና ዴታዎችን ከተለያዩ ምንጮች በማሰባሰብ፤በመረጃ ቋት የማስቀመጥ ስራዎችን ይሰራል፡፡አገራዊና አህጉራዊ የህብረተሰብ ጤና ክስተቶች በተመለከተ የዳታ ልውውጥ ስርዓት ለመዘርጋት ይሰራል፤የጤና ዳታ/መረጃ የማጋራትና ስርዓት የመዘርጋት፤ የመረጃ ደህንነትና ሚስጥራዊነትን መጠበቅ ስራዎችንም ይሰራል፤የተለያዩ የዳታ ስርዓቶችን ለማናበብና መስተጋብር የመፍጠር ስራም አንዱ ዋና ትኩረቱ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመረጃ ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ስርዓት የመዘርጋት ዓላማም ይዞ ነው እየሰራ ያለው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የጤና መረጃ ስርዓቱን ማዘመንና የዳታ ተደራሽነት የማሳለጥ ስራን የሚያከውን ሲሆን፤የላቀና ዘመኑን የዋጀ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የጤና ዴታ ቀመርን ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ይሰራል፡፡ በሌላ በኩል የስታትስቲክስና የሂሳብ ቀመሮችን እንዲሁም ዳታ ሳይንስ (Data Science) በመጠቀም ለጤናው ዘርፍና ለህብረተሰብ ጤና ገላጭ የሆኑ ቀመሮችን ሰዎች በቀላሉ በሚረዱት አቀራረብና መረጃውንም በቀላሉ የሚያገኙበትን የሞዴሊንግ ትንበያ ስርዓትን በመዘርጋት ተደራሽ የማድረግ ስራዎችም ይሰራል፡፡በተጨማሪ በአገር አቀፍ ደረጃ ጤናና ጤና ነክ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመከታተል በመገምገምና ከፍተኛ ጥራት ያላቸዉ ሳይንሳዊ ትንተናዎችን ያዘጋጃል፤ እንዲሁም በሃገሪቱና በክልሎች ውስጥ ያለውን የበሽታ ምጣኔ በዕድሜ፣ በፆታና በአመት በማጥናት ማስረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔ ሰጪነት ላይ ያለዉን ክፍተት ለማጥበብ ይሰራል፡፡
ጥ- ማዕከሉ ከተቋቋመ በሁዋላ ምን ተግባራትን አከናወነ?
ማዕከሉን ስራ ለማስጀመር ጠንካራ የመረጃ ትንተናና የቅመራ ቡድን ማዋቀር አስፈላጊ ነበር፡፡ ቡድኑን ከማዋቀር በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲዎች፤በአጋር ድርጅቶች፤በሴክተር መስሪያ ቤቶች፤ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተሰሩትን ዳታዎች ፈልጎ ማግኘት፤ምን አይነት ዳታ እንዳለ ማወቅና ማሰባሰብ ሌላው ስራ ነበር፡፡እስካሁን በማዕከሉ የተሰራው የዳታ ሃብትን ማወቅ፤ምን አይነት ዳታ እንዳለ መለየት፤ የት እንዳሉ ማሰስ፤በምን አይነት አያያዝ ላይ እንዳሉ ማጥናት፤ ፤ለትንትናና ለቅመራ የሚያስፈልጉ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ አሰራርን በማጥናት ላይ ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡ከዚህ በተጨማሪም ዳታዎቹን ከአንዱ ወደአንዱ ለማስተላለፍ የዳታ-ማጋሪያና መቀባበያ ግልጽ መመሪያዎችን ማዘጋጀትም ይጠይቅ ነበርና በርካታ የአሰራር መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በሌላ በኩል በተለያየ ዘርፍና ሙያ የሚገኙና ብቃትና እውቀት ያላቸው በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በመፈለግ ቡድኑን በሰው ሃይል የማጠናከር ስራ ተሰርቷል፡፡
ጥያቄ- በአገራችን በተለይ ከጤናና ጤና ነክ ዳታዎች ጋር በተያያዘ ከዳታ አያያዝና አስተዳደር ጋር የሚነሱ ዋና ዋና ችግሮች ምን ነበሩ?
ዶ/ር ዓለምነሽ – ይታዩ የነበሩ ችግሮችን በሶስት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡የመጀመሪያው የሚሰሩ ምርምሮችና ዳታዎች በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ ልምድ አለመኖሩ ተጠቃሽ ነው፡፡ለምሳሌ አንድ ጥናት ከተሰራ በሁዋላ የዳታ ባለቤትነት ጉዳይ ሲነሳ የሚሰሩ ጥናቶች የኢንስቲትዩቱ ሳይሆን የተመራማሪው የራሱ የግሉ ንብረት አድርጎ የማየት ልምድ ነበር፡፡ስለሆነም ይህን የባለቤትነት እሳቤ ለማስተካከል የዳታ ማጋሪያ መመሪያዎችን በማሻሻልና በማዘጋጀት ዳታዎችን ወደአንድ ቋት ለማከማቸት በቅድሚያ አዲስ አስተሳሰብና አዲስ ባህል ማስተዋወቅ ያስፈልጋልና ይህን ለማምጣት ብዙ ርቀት ሄደናል፡፡እንደ ኢንስቲትዩት ደግሞ ዳታዎችን ከሌላ ተቋም ስናመጣ የምንረከብበት አሰራር አልነበረንም፤ በመሆኑም ይህን ክፍተት የሚያስተካክል የመግባቢያ ሰነድ አዘጋጅተናል፡፡መመሪያም እየተዘጋጀ ነው፡፡
ሌላው ችግር ዳታዎች የሚቀመጡበት የዳታ መሰረተ-ልማት(መዋቅር)አልነበረም፡፡ይሄ ትልቅ ፈተናም ነበር፡፡የኢንተርኔት አቅሙ፤መሰረተ-ልማቱ፤ለስራው አጋዥ የሆኑት ቁሶች፤የሶፍትዌርና ሃርድዌር አቅሙ በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ ይህን ትልቅ ስራ የሚያስተዳድርበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አቅምና ብቃቱ መፈተሽ ነበረበት፡፡ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የአይቲ ኦዲት ሰርተውልናል፤ ይህ ቴክኖሎጂ ነክ ዳሰሳ ከተጠና በሁዋላ ለዚህ ስራ አስፈላጊ የሆነ የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት የማስተካከል ስራ ፈታኝ ቢሆንም ተሰርቷል፤የመሳሪያ ግዥና ተያያዥ ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡በዚህ መስረት ከፍተኛ አቅም ያለው ሰርቨር እና የዳታ ሴኩውሪቲውን ለማጠናከር አስተማማኝ ደህንነት መፍጠር፤ዳታ ሴኩሪቲን የሚያግዝ ገዥ መመሪያ የማዘጋጀት እና በቀላሉ በኔትወርክ ዳታ የሚገኝበትን አሰራር በመዘርጋት ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡ወደ 8 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚያወጣ የዳታ መሰረተ- ልማት ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት እያደረግንም እንገኛለን፡፡
ዶ/ር አወቀ- እንግዲህ ከላይ እንደተገለፀው አዲስ የዳታ ስርዓት መፍጠር በጣም ከባድ ጥረት ይጠይቃል፡፡ተመራማሪዎች ኢንስቲትዩቱን ለቀው ሲሄዱ የሰሩትን የምርምር ስራ ዳታ ሳያስረክቡ የመሄድ ልምድ ነበር እናም ዳታዎችን ለመረከብ በጣም ከባድ ፈተና ነበረብን፡፡የዳታ ሳይንስን ተረድቶና ለሌሎችም ግንዛቤውን ፈጥሮ የአይቲ መሰረተ-ልማቱን ማቀድና ማዘጋጀትም ትልቅ ስራ ይጠይቃል፡፡በርካታ ውይይቶች፤ስምምነቶች፤አሰራሮች፤ስትራቴጂክ ፕላኖች፤ የመግባቢያ ሰነዶች፤የተለያዩ መመሪያና አሰራሮችን መፈተሸና ማዘጋጀትን ይጠይቅ ነበር፤ፈተናም ያየንበት ነው፡፡ እንደግለሰብም እንደቡድንም ስለለውጥ የተማርንበት አጋጣሚ ነው ለማለት እችላለሁ፡፡በዚህ አጋጣሚ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉትን ዶ/ር ኤባን ጨምሮ ዶ/ር ዓለምነሽን፤የየክፍሉን የስራ ሃላፊዎች፤ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲን ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
የሰው ሃይል ማሟላቱም ሌላው ፈተና ነበር፤የስራውን ባህሪና ፍላጎት የተረዳ ባለሙያ በመፈለግ ቀጥረናል፤በአሁኑ ወቅት 36 ባለሙያዎች በማዕከሉ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ በማስተካከል ማዕከሉ ስራ ጀምሯል፡፡
ጥያቄ- ማዕከሉ ስራ ከጀመረ በሁዋላ በአራት ንዑስ ክፍሎች ተደራጅቶ ስራ ጀምሯል፤ እስኪ ስለእነዚህ ክፍሎች ዓላማና ተግባር አብራሩልን?
ልክ ነው፤ማዕከሉ በአራት ኬዝ ቲሞች ተዋቅሯል፡፡በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡፡
- የጤና የዳታ ክምችትና አስተዳደር ቡድን (Health Data Repository and Governance case team)
የዚህ ኬዝቲም ዓላማ የጤና ዳታዎችና መረጃዎች ከተለያዩ ምንጮች በማሰባሰብ፤ደረጃውን የጠበቀ የመረጃ ቋት ማዘጋጀት፤ማደራጀትና የመረጃ ጥራትን ማረጋገጥ ነው፡፡ በተጨማሪም አገራዊና አህጉራዊ እንዲሁም አለምአቀፋዊ ዲጂታል የጤና ዳታ ስርዓት በመዘርጋትና መስተጋብር በመፍጠር የዳታ ልውውጥን ማሳለጥ እንዲሁም የዳታ ማጋራት እና የመጠቀም ባህልን ማሳደግ ነው፡፡
- የጤና ዳታ ቅመራ ሞዴሊንግ እና ቪዥዋላይዜሽን ኬዝ ቲም (Health Data Analytics, Modeling and Visualization case team)
የዚህ ኬዝቲም ዓላማ የላቀና ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂዎችን ለምሳሌ ያህል እንደ ሰዉ ስራሽ ብልሀት (Artificial intelligence, machine learning, data mining) በመጠቀም የጤና ዳታ ቅመራን ከፍተኛ ደረጃ ማድረስ ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ የሞዴሊንግ ትንበያ፤ የረቀቁ የስታትስቲክስና የሂሳብ ቀመሮችን እንዲሁም ዳታ ሳይንስ (Data Science) በመጠቀም ለጤናው ዘርፍና ለህብረተሰብ ጤና ገላጭ የሆኑ ቀመሮችን ሰዎች በቀላሉ በሚረዱትና በቀላሉ የሚያገኙበትን ስርዓት በመዘርጋት ተደራሽ ማድረግ
- የጤና ማስረጃ ትንተናና ስርጸት ቡድን (Health Evidence Synthesis& Translation case team)
ይህ ኬዝ ቲም ሁለት ዓላማዎች አሉት፤
1.የጤናና ጤና ነክ ፖሊሲዎችን ስትራቴጂዎችን ፕሮግራሞችን ትግበራና ውጤታማነት መረጃና ማስረጃዎችን በማጠናቀር ክትትል፤ ግምገማ፣ እንዲሁም ትንተና በማድረግ ለጤናው ዘርፍና ለህብረተሰብ ጤና አስፈላጊውን የማስረጃ ግብዓት መስጠት
- በማዕከሉ የተተነተኑ ማስረጃዎች ጥቅም ላይ ይውሉ ዘንድ የተለያዩ ስርዓቶችን በመዘርጋት ለፖሊሲ አውጪና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግና የመረጃ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የበሽታዎች ጫናና ስርጭት (Burden of Diseases case team)
የዚህ ኬዝቲም ዓላማ በአገርአቀፍ፤በክልልናበወረዳ ደረጃ የበሽታዎችንና አጋላጭ መንስኤዎቻቸው የሚያደርሱትን ጫናና ስርጭት ህልፈተ ህይወት እንዲሁም ያለዕድሜ መቀጨት በጊዜ፣በፆታ ፣በዕድሜ ሳይንሳዊ አሰራርን ተከትሎ ጥናቶችን ማካሄድና ልኬቶች ማቅረብ ነው፡፡
ጥ- እስካሁን ምን ያህል ዳታዎችን ለመሰብሰብ ተችሏል?
ዶ/ር ዓለምነሽ – እስካሁን ካነጋገርናቸው 60 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ 40 ያህሉ ዳታ ሰጥተውናል፡፡በክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ውስጥ ያሉ ዳታዎችንም ሰብስበናል፡፡ቀደም ሲል የኢንስቲትዩቱ ባልደረባ የነበሩ ባለሙያዎች ነገር ግን አሁን ተቋሙን ለቀው የሄዱ በርካታ ተመራማሪዎች አሉ፤ከእነሱ ጋር በመፃፃፍ ዳታ እንዲሰጡን አድርገናል፡፡ከሴሮ እና ከፕላን ክፍል ጋር መረጃ በመሰብሰብ ዳታ የሌላቸውን ቴክኒካል ሪፖርት ለማሰባሰብ ጥረት አድርገናል፡፡በኢንስቲትዩቱ ከጥንት ጀምሮ የታተሙ ከ 1700 በላይ የምርምር ህትመቶችንም አከማችተናል፡፡አሁን የዳታ ጥራትን ለማምጣት እየሰራን ነው፡፡ እስካሁን ከተሰበሰቡት ዳታዎች ውስጥ ለ 272 ዳታ ሴቶች አጭር መግለጫ ተዘጋጅታል
ጥ- ለመሆኑ የጤና ዳታ ሲባል ምን አይነት ዳታዎችን ያካትታል?
ዶ/ር ዓለምነሽ- የጤና ዳታ ብዙ ነገሮችን ይይዛል፤በጣምም ሰፊ ነው፡፡ጤና ማለት በባሕሪው ከብዙ ሴክተሮች ጋር ስለሚገናኝ ጤናና ከጤና ጋር ተያያዥ የሆኑ የሜትሮሎጂ፤የትራፊክ፤ግብርና፤ምግብ፤ የሞትና የልደት መጠኖችና መሰል ዳታዎችን ያካትታል፡፡
ጥ- ማእከሉ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም እስካሁን ከተሰሩ ስራዎች ውስጥ እንደስኬት የሚነሳ ተግባር አለ?
ዶ/ር አወቀ-እንደ ኢንስቲትዩት ትልቅ ስኬት አስመዝግበንበታል ብለን የምንገልፀው ተግባር የዳታ ማከማቻና አስተዳደር ስራ መስራታችን ነው፡፡በመጀመሪያ የሰራነው በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ባለፉት አስርት ዓመታት ምን ያህል ዳታዎች ተሰብስበዋል የሚለውን ቆጠራ አካሄድን፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች፤ በግል አማካሪዎች የተሰሩትን ለማየት ሞክረናል፤ይህም የሚጠቀስ ስኬት ነው፡፡በአፍሪካ ደረጃ ጠንካራ ስራ እየተሰራ ነው ያለው፡፡ስራው ሰፊና አድካሚ ቢሆንም ያሉት ባለሙያዎች ጠንካራ በመሆናቸው እያሳካነው ነው፡፡
ይህን ማዕከል በምስራቅ አፍሪካ በበሽታ ጫና መረጃ ቅመራ ረገድ የልህቀት ማእከል ለማድረግ ከአፍሪካ ሲዲሲ ጋር በቅርበት እየሰራን ነው፡፡የዓለም ጤና ድርጅትም ይህን ስርዓት ያደነቁት ሲሆን ፤እንደካናዳ ያሉት አገራትም ሳይቀር ያደነቁት ነው፡፡ለአፍሪካም ሞዴል የሆነ ስራ እየሰራን ነው የምንገኘው፡፡
ጥ-የማዕከሉ መመስረት ምን ጠቀሜታ አለው?
ዶ/ር ዓለምነሽ- የዚህ ማእከል መመስረት የኢንስቲትዩቱን ገጽታ በጣም ቀይሮታል፡፡በተለይ በተለያዩ አጋር አካላት የተሰሩ ዳታዎች በአግባቡ ተቀምረውና ተሰናድተው ለሚፈልጉት አካላት ስለማይደርስ ብዙ አጋሮች ደስተኛ አልነበሩም፤በዚህ ምክንያትም የምርምር ድጋፍ ያቋረጡም አሉ፡፡ሌላው ቢቀር የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንኳን ዳታ ለመጠየቅ ወደኢንስቲትዩቱ መምጣት አይፈልጉም ፤ምክንያቱም የሚፈልጉትን ዳታ ስለማያገኙ ነው፡፡ይህ ማእከል በመቋቋሙ እንግዲህ ቅሬታ የነበራቸው አጋር አካላትና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጥያቄያቸውን በአግባቡ የሚመልስ ተቋም መገንባቱ አስደስቷቸዋል፡፡በመሆኑም አሁን በብዛት የዳታ ጥያቄዎች እየቀረቡልን ነው፡፡በሳምንት ሶስት የሚሆን ጥያቄ እየመጣ ነው፡፡አገልግሎቱን በፍጥነት ለመስጠት አሰራሮችን አመቻችተናል፡፡በዚህም መሰረት በጥቂት ቀናት ለምሳሌ በሁለት ቀናት፤ምናልባት ማጣራት የሚያስፈልገው አገልግሎት ከሆነ በሳምንት ጊዜ አለዚያ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ መልስ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ዳታሴቶች በኦንላይን ገብተው በማየትና የሚፈልጉትን አገልግሎት ወስነው በማመልከት ፈጣን አገልግሎት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
ጥ- የዳታ ብልሽት፤ጉዳትና መጥፋት ምናልባት ስርቆትንም ለመከላከል ምን አይነት ጥንቃቄዎች ይደረጋል?
ዶ/ር ዓለምነሽ/ዶር አወቀ- ዓለምአቀፍ ስታንዳርድ በመከተል የዳታ ደህንነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ጥንቃቄዎች ይደረጋሉ፡፡ለምሳሌ በየሁለት ሰዓቱ ባክአፕ ይያዛል፤የዳታ ማጋሪያ ስምምነቶች በጥንቃቄ የተቀመጡ አሰራሮች አሉ፡፡በባህላዊ መንገድ የሚኬበትን የቀድሞ አሰራር አስወግደናል፡፡
ጥ- መረጃን በማምረት ለፖሊሲ አውጭዎችና ለፕሮግራም አስፈፃሚዎች በማድረስ ረገድ ምን ያህል ስኬታማ ስራ ተሰርቷል?
ዶ/ር ዓለምነሽ-ማዕከሉ ያዘጋጃቸው መረጃዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጥቅም ላይ ሲውሉ እናያለን፡፡የዓለምአቀፍ የበሽታ ጫናን በተመለከተ መረጃዎቹን በተለያዩ ዶክመንቶች ላይ አካተው እየተጠቀሙባቸው ነው፡፡ባይሆን የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች በተጠበቀው መልኩ ከማዕከሉ ተጠቃሚ አለመሆናቸው ቅር ያሰኛል፤ግን የማእከሉን አገልግሎቶች ሲረዱ ወደማእከሉ በመምጣት ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡
ዶ/ር አወቀ-የዳታ ጥያቄዎችን በተመለከተ ያደረግነው ዳሰሳ ያሳየን እውነታ ቢኖር ዳታን በተመለከተ ተቋማት የየራሳቸውን ባህል ተከትለው እንደሚሰሩ ነው፡፡ለምሳሌ በጋራ ስለመስራት፤ዳታን በጋራ ስለማስተላለፍ ውስንነት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡በብዛት ዳታዎች በተለያየ ዘርፍ ቢኖረን ይህን ለማስተናገድ የሚያስችል የብቃት ችግርም አለ፡፡ዳታና የዳታ አሰራርን የመረዳት ችግር፤ለውጥን የመረዳትና ለለውጥ ዝግጁ የመሆን ችግሮች ቢታዩም ይህ ማእከል አዲስ ባህልን ለማስተዋወቅና እንደ ባህል ለማስረጽ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ለምሳሌ የበሽታ ጫና መረጃና ትንተናን በተመለከተ የትኛው የበሽታ አይነት ብዙ በጀት ይፈልጋል? የትኛው ክልልስ የበለጠ የበሽታ ጫና አለበት? በሚል ሳይንሳዊ ጥናት ሰርተን እያሳየን ነው፡፡እንዲህ አይነት መረጃዎች ለውሳኔ ምቹ በመሆናቸው የበጀት ፍትሃዊ ድልድልና ምደባን ያግዛሉ፡፡በሳንባ ነቀርሳላይ፤ያለእድሜ የሚሰከት ሞትን፤በጨቅላ ህፃናትና በእናቶች ላይ፤በቤት ውስጥ የአየር ብክለትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ መረጃውን በማጠናቀር ከኢንስቲትዩቱ የሚጠበቀውን ጥናታዊ መረጃ እየሰራን ነው፡፡ከዚያም በተለያዩ ሳይንሳዊ መጽሄቶች ለምሳሌ እንደ ላንሴት ባሉ መጽሄቶች የምናሳትም ይሆናል፡፡ የጤና ሚኒስትር ባወጣዉ የጤና ትራንስፎርሜሽን ላይ ያሉ ወደ መቶ ጠቃሚዎቸን (ኢንዲኬተሮችን) ለመመርመርም እቅድ ይዘናል፡፡
ጥ-ስለአጋርነት ከተነሳ አይቀር ማዕከሉ በዚህ ረገድ ምን አከናውኗል?
ማዕከሉ ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አጋሮች ጋር በቅርበት ይሰራል፡፡ ከኢንስቲትዩቱ ውጭ አብረውን በጋራ የሚሰሩ እስከ 700 የሚሆኑ ሰዎችና ተባባሪዎችና አጋሮች አሉን፡፡ከዚህ ውስጥ 400 የሚሆኑት ከእኛ ጋር በእኛ ሲስተም ለመስራት ተስማምተዋል፡፡ከአጋሮች በተለይ ከአፍሪካ ሲዲሲ፤ከአዲስ አበባ፤ ከጅማና ጎንደር ዩኒቨርሲዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለን፡፡ከዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ፤አውስትራሊያ ካሉ ዲያስፖራ ወገኖች ጋርም እየሰራን ነው፡፡ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ማእከሉንና የምንሰራውን ስራ በማስተዋወቅ ላይ ስንሆን፤ የጤና ጥበቃና የሴክተር መስሪያ ቤቶች አማካሪዎችን ጨምሮ በርካታ አጋሮቻችን እየተሰራ ያለውን ስራ በማድነቅ ትልቅ ክፍተት እየሞላችሁ ነው ብለው አበረታች አስተያየት ሰጥተውናል፡፡
ጥ- የተለያዩ ተመራማሪዎች ለምርምር ስራ ወይም ለፕሮግራም ቀረፃ የሚያግዙ የዳታ ጥያቄዎች ሲመጡ ለማስተናገድ ያለው አሰራር ምን ይመስላል? መስፈርቶቹስ ጋባዥ ናቸው?
ዶ/ር ዓለምነሽ-የዳታ ማጋሪያ ሂደቱ በጣም አጥሯል፤ መስፈርቶቹም ተከልሰዋል፡፡ለምሳሌ ለፕሮግራም የሚፈለጉ ዳታዎችን ለመውሰድ ከ መስሪያ ቤታቸው ደብዳቤ በመያዝ ይመጣሉ፤ ከዚያም ማእከሉ ዳታው መኖሩን ፤ጥናቱ ዓመት መሙላቱን በማረጋገጥ አስፈላጊውን ማጣራት አድርገን ማጋራት እንችላለን፡፡ለምርምር ከሆነ ደግሞ ተጨማሪ የምርምር ስነ ምግባር(አይ.አር.ቢ) ደብዳቤ በመያዝ ኦንላይን ማመልከቻውን በመሙላት በፍጥነት በሳምንታት ውስጥ ሊስተናገዱ ይችላሉ፡፡
ጥ- ማዕከሉ የወደፊት እቅዱ ምንድነው?
ዶ/ር ዓለምነሽ-እኛ እንደአፍሪካ ነው ጎልተን መውጣት የምንፈልገው፡፡የተጀመሩ ስራዎች አጠናክረን በመስራት ፍሬ ማፍራት አለባቸው፤ሌሎቹ ስራዎች ለምሳሌ የክልል የዳታ ሃቦችን የማስጀመር ስራዎች ይሰራሉ፤የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት የሚለውን በተግባር ሰርተን ማሳየት እንፈልጋለን፡፡ትልቅ ዓላማ አለን፡፡
ዶ/ር አወቀ- አብሮ በጋራ መስራት እና የአቅም ግንባታ ስራዎችም ዋናው ትኩረታችን ነው፡፡ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደማእከላችን በማምጣት መስራት እንፈልጋለን፡፡ዳታን በተመለከተ የግለሰቦችን፤የኢንስቲትዩቱንና፤የአገሪቱን ምክንያታዊ ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቅ ዋናው ትኩረታችን ነው፡፡ሌላው ራእያችን እንደአገር ብዙ አስተዋጽዖ ማበርከት የምንፈልግበት ጉዳይ ቢኖር ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተመሳሳይ ስርዓት እንዲፈጥሩ ምሳሌ ሆነን የማእከሉን ተመሳሳይ ስራዎች ማባዛት፤ በአፍሪካ ደረጃ ምሳሌ የሆነ ማእከል መፍጠርን እናልማለን፡፡ለአፍሪካ ሲዲሲ ቴክኒካል ክንፍ ሆነን አፍሪካን ማገዝ እንፈልጋለን፡፡
ስለነበረን ቆይታ በኢንስቲትዩቱ ስም እናመሰግናለን፡፡