የብሔራዊ መሰረታዊ የህክምና ላብራቶሪ ምርመራ ዝርዝር ሰነድ ዝግጅት አዉደ-ጥናት ተጀመረ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት እና አጋር ድርጅቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ብሔራዊ የቴክኒካል የስራ ቡድን በተገኙበት ታህሳስ 24/2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የብሔራዊ መሰረታዊ የህክምና የላብራቶሪ ምርመራ ዝርዝር ሰነድ ዝግጅት አውደ ጥናት አስጀመረ።
የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ የብሔራዊ የቴክኒክ ሥራ ቡድኑን (NTWG) በይፋ ለማቋቋም፤ የመረጃ መሰብሰቢያ መጠይቁን በመገምገም እና የሚነሱ አስተያየቶችን በማዳበር ለማጠናቀቅ እንዲሁም ለሙከራ እና ለመረጃ እይታ እንዲረዳ ከጤና ተቋማት ኦዲኬ መሰብሰብያውን (ODK format) በመጠቀም መረጃን ለመሰብሰብ እና ዶክመንት ማዘጋጀት ነው።
አቶ ዳንኤል መለሰ የኢንስቱትዩቱ የብሔራዊ ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ አንደተናገሩት የብሔራዊ መሰረታዊ የህክምና የላብራቶሪ ምርመራ ዝርዝር ሰነድ ተዘጋጅቶ በሃገር ውስጥ በመተግበር የመሰረታዊ የህክምና ላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ፤ የላብራቶሪዎችን የምርመራ ሽፋን ለማሻሻል እና ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተመረጡ የጤና ተቋማት ላይ በቀጣይ የሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት አሁን ያሉበትን ደረጃ በግልፅ መረዳት እንዲቻል የሚያግዝ መሆኑን፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የመሰረታዊ የህክምና ላቦራቶሪ ምርመራዎች ዝርዝር ለሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም የአገር በቀልና ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶችን ጥረት እና ያሉትን መሠረተ ልማቶች ሁሉን አቀፍ ለሆነ የጤና ሽፋን ለማሟላት የሚያግዝ መሆኑን አቶ ዳንኤል አያይዘው ተናግረዋል፡፡
የሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት የመሰረታዊ የህክምና ላብራቶሪ ምርመራ መገኘት እና ተደራሽነት፣ ወቅታዊ የበሽታ ስርጭት እና ልዩነቶች፣ የሰው እና የፋይናንሺያል ሀብቶች አቅም እንዲሁም አስፈላጊው የመሠረተ ልማት አቅርቦትን በተመለከተ መረጃ የሚሰበሰብ ሲሆን የሚገኘው መረጃ ለብሔራዊ መሰረታዊ የህክምና ላብራቶሪ ምርመራ ዝርዝር ሰነድ ዝግጅት (NEDL) ወሳኝ ግብአት ሆኖ እንደሚያገልግል ከአው ደጥናቱ አስተባባሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡
የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት፣ የኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የስራ ክፍል ባለሙያዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ፣ የአጋር ድርጅቶች እና የሞያ ማህበራት ተወካዮች በአውደ ጥናቱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡