የአብክመ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ”National Information Platform Nutrition (NIPN)” ፕሮጀክት ጋር በትብብር ለመስራት የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፕሮጀክቱን ወደ አማራ ክልል አውርዶ ለመስራት ጥቅምት 21 አስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተዘጋጀው ወርክሾፕ ላይ የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በስምምነቱ ላይ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ከስርዓተ – ምግብ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ችግር በምርምር ለመፍታት የሚሰራ ሲሆን ኢንስቲትዩቱ የተቀበለውን ሃላፊነት በተሻለ ደረጃ እየተወጣ እና ወደ ክልሎች ለማድረስ እየሰራ ነው ብለዋል።
የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ክልሎችን ለማጠናከር እየሰራ ያለው ስራ ጥሩ መሆኑን ገልፀው ፕሮጀክቱ ክልሉ አብሮ እንዲሰራ እድሉ በመፈጠሩ ምስጋና አቅርበዋል።
የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ ከሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ የመስራት ልምድ እንዳለው ያስረዱት አቶ በላይ የክልላችንን የስርዓተ – ምግብ ችግር ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥተን ተቋማትን አቀናጅተን በመስራት በውጤት እንገናኛለን ብለዋል።
በመድረኩ የፕሮጀክቱ አስተባባሪና መሪ ተመራማሪ ዶ/ር አረጋሽ ሳሙኤል በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ተግባራትን ያቀረቡ ሲሆን መረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔ እንዲሰጥ ተመራማሪዎችንና ውሳኔ ሰጪ አካላትን ማገናኘት የፕሮጀክቱ ዓላማ እንደሆነ አስረድተዋል።
ዶ/ር አረጋሽ አክለውም ፕሮጀክቱን ወደ አማራ ክልል በማውረድ ወደ ስራ ለማስገባት የመጀመሪያ እንደሆነ ገልፀው በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ተቋማት በቅንጅት በመስራት ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
በአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍቅርተ እስጢፋኖስ በመድረኩ ኢንስቲትዩቱ ፕሮጀክቱን የመፈፀም ዝግጁነት፣ አቅም እና መልካም ተሞክሮዎችን እንዲሁም የኢንስቲትዩቱን ዓላማ እና የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራትን
የሚያሳይ ሰነድ አቅርበዋል።
ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጀው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ካሉት 27 የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ዘጠኙ ስርዓተ-ምግብ ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ወ/ሮ ፍቅርተ አብራርተዋል።
የአብክመ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተቀበለውን ሃላፊነት መፈፀም የሚችል መሆኑ እምነት እንዳላቸው የተናገሩት ዶ/ር ጌታቸው በጋራ በመስራት ለክልልም ሆነ ለአገር የሚጠቅም ስራ መስራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።