የአደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል በለሙያዎች ከመጋቢት 21- 26/2014 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል
April 7, 2022
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቅድመ ማስጠንቀቅያና መረጃ ስርዓት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበርያ (PHEOC) እና የክስተት አስተዳደር ስርዓት (IMS) ዙሪያ ለሶስተኛ ዙር ባካሄደው ስልጠና ለክልል ጤና ቢሮዎች/ጤና ኢንስቲትዩቶች፣ ለዞን ጤና መምሪያዎች፣ ለሀገር መከላከያ ጤና መምሪያ፣ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጤና መምሪያ እንዲሁም ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እና የአደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል በለሙያዎች ከመጋቢት 21- 26/2014 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል።
ስልጠናው የሕብረተሰብ ጤና አመራሮችና ባለሙያዎች መረጃን እና ሀብቶችን በብቃት አቀናጅቶ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን በፍጥነት ለማስተባበርና ለመቆጣጠር እንዲቻል ግንዛቤ የሚያሳድግ ነው፡፡ ከዚህ ስልጠና በተጨማሪ ተሳታፊዎቹ የሲዳማ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበርያ ማዕከሎችን (PHEOCs) እንዲጎበኙ የተደረገ ሲሆን የጉብኝቱ ዓላማ በስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ለማዳበር ብሎም የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ለማስቻል ነው።
በስልጠናውም የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ እንዳሻው ሽብሩ የእንኳን ደህና መጣቹና የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቅድመ ማስጠንቀቅያና መረጃ ስርዓት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ አሰፋ ከአፍሪካ ሲዲሲ ተወካይ በተገኘበት የመዝጊያ ንግግር በማድረግ ስልጠናውን በብቃት ላጠናቀቁ ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት አበርክተዋል።