የኢቦላ በሽታ ከመከሰቱ አስቀድሞ ለመከላከል የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ
የኢቦላ በሽታ ለከባድ ህመም የሚዳርግና በኢቦላ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ በሽታው በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን በበሽታው ከሚያዙት ውስጥ እስከ 90 በመቶ የሚደርሱት የህክምና እርዳታ ካልተደረገላቸው ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ ሆኖም በበሽታው ከተያዙት መካከል ተጓዳኝ እርዳታ ከተደረገላቸው 52 ፐርሰንት የመዳን እድል ይኖራቸዋል፡፡ የኢቦላ በሽታ ከዚህ በፊት ክትባት ያልነበረው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በተወሰነ መልኩ በአገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ በሽታው ይህ ነው የሚባል ፍቱን ህክምና ያልተገኘለት ከመሆኑም በላይ በሽታው በአለማችን ካሉ አደገኛ ከሚባሉት በሽታዎች መከከል አንዱ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ በአዲስ መልክ የተከሰተ መሆኑ ይታወቀል፡፡ በሽታው ወደ ሌሎች አጎራባች አገራት እንዳይዛመት ለመቆጣጠርና ለማጥፋት የሃገሪቱ መንግስት፣የአለም ጤና ድርጅትን እና በርካታ አጋር ድርጅቶችን ጨምሮ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም በሽታው በአሁኑ ሰዓት ለአለም የሚያሰጋ ችግር ሆኖ በማይታይበት ደረጃ ላይ በማድረስ በቁጥጥር ስር እየዋለ ይገኛል፡፡ ሃገራችን ኢትዮጵያም ገና ከጅምሩ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ ሲከሰት የብሔራዊ የኢቦላ አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም የኢቦላ ወረርሽኝ ዝግጅትና ምላሽ አሰጣጥ ሀገራዊ እቅድ በማዘጋጀት ከፍተኛ የሆነ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ከቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴዎች መከከል አንዱ የጤና ባለሙያዎችን ስለ ኢባላ ያላቸውን እውቀት በተለይም በሽታውን ከመከላከል አንጻር፣በበሽታው የተያዙትን እንዴት መርዳት እንደሚቻልና ተላላፊነቱን ለመግታት የሚደረጉትን ጥንቃቄዎች ላይ የእውቀት ግንዛቤን በሚገባ ከፍ ለማድረግ የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማእከል ለከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 2/2010 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በሊሳክ ሪዞርት ኢቦላን አስመልክቶ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የስልጠናውም ዋና ዓላማ ኢቦላን ለመከላከል በሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ከኢትዮጵያ መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተውጣጡ እና ኢቦላን ለመከላከል ዘምተው የተመለሱ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በማካተት የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት የክልል ባለሙያዎችን በስራቸው ያሉትን እንዲያሰለጥኑ ለማድረግ የተዘጋጀ ስልጠና ነው፡፡
ስልጠናው በኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች እና በአለም አቀፍ ጤና ድርጅት ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ስልጠናው በጥያቄና መልስ፣በፊት ለፊት ገለጻ ከመሰጠቱም በላይ ኢቦላ በኢትዮጵያ ቢከሰት ወይም ጥርጣሬ ቢፈጥር በችግሩ የተጠረጠሩ እና በሽታው የተገኘባቸውን ለማከምና ለማቆያ በተዘጋጀው በቦሌ ጨፌ ጤና ጣቢያ ባለሙያዎች ተገኝተው በተግባር ስልጠናውን ወስደዋል፡፡
በተግባሩ ስልጠና ወቅት ሰልጣኞች በሽታውን ለመከላከል የሚለበሰውን ልብስ ከመጀመሪያ አለባበስ እስከ ማውለቅ ደረጃ ያሉትን እንዲሁም በበሽታው የተያዘውን እና የተጠረጠረውን ግለሰብ በመርዳት ደረጃ የሚደረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄዎችን ስለማድረግ በጥልቀት ለባለሙያዎቹ ተሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም ከስልጠናው መጠናቀቅ በኋላ ስለማቆያው ቦታ ዝግጅት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከሰልጣኞች በተለይም ኢቦላን ለማጥፋት ከዘመቱ ባለሙያዎችና ከአለም አቀፍ ጤና ድርጅት ባለሙያዎች መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ጥቆማና እጅግ ገንቢ የሆኑ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር የአስቸኳይ ማስተባበሪያ ማእከል (EOC) አስተባባሪ (Incident manager) የሆኑት አቶ ዘውዱ አሰፋ የማጠቃለያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የተሰጡትን አስተያየቶች እና ጥቆማዎች በሚገባ በመቀበል መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች በአፋጣኝ እንደሚስተካከሉ ከመናገራቸውም በላይ ስልጠናወን ለወሰዱ ባለሙያዎች በቀጣይ ስልጠናው ወደ ክልል በሚወርድበት ወቅት ትልቁን የማስተባባር ድርሻ መውሰድ እንዳለባቸው፣ በበሽታው የተጠረጠረ ቢገኝ በማንኛውም ጊዜ ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጁ መሆን እንዳለባቸውና የማከሚያው ወይም የማቆያው ማእከል ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እንዲሁም በክልሎች በሚቋቋምበት ጊዜ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በአጠቃላይ እንደሃገር ይህንን አስከፊ በሽታ አስቀድሞ ለመከላከል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሲሆን በቀጣይም ለክልል ሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማእከል፣ለክልል መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ባለሙያዎች እና ኢቦላ ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡