የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ስምምነት ተፈራረመ
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለውን የስራ ግንኙነት ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠልና የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች የባንክ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ፕሮግራም በዛሬው እለት አከናወነ፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር በዝግጅቱ ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ተቋሙ የሀገራችንን ህዝብ ጤና ለመጠበቅ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ውስጥ ችግር ፈች የምርምር ስራዎችን በማካሄድ እንዲሁም እንደ ኢቦላ እና የኮቪድ 19 አይነት የህብረተሰብ ጤናና ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ እንዲሁም የቁጥጥር እና ምላሽ ስራዎችን በማከናወን ታላቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት የጤና ጥበቃ የቴክኒካል ክንፍ የሆነ ተቋም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የተዘጋጀው የብድር ስምምነትም ለኢንስቲትዩት ሰራተኞችም ሆነ ለተቋሙ የሚሰጠው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አቶ ግሩም ከበደ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመርካቶ ዲስትሪክት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸው ኢንስቲትዩቱንም ሆነ ሰራተኞቹን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ መርሀ ግብር እውን በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ባንኩ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማከናወን ያለውን ቁርጠኝነት አሳውቀዋል፡፡
ይህ ስምምነት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሰራተኞች የብድር አገልግሎት እንዲመቻችላቸው እና ያለባቸውን የመኖሪያ ቤትና የተለያዩ ፍላጎቶች ለማሟላት ብሎም የሰራተኞችን እርካታ ለመጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡