የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአለም አቀፍ ደረጃ የተከናወነ የጥናትና ምርምር ውድድርን አሸነፈ
ለምርምር ስራዎች የሚሰጠው ትኩረት እያደገና እየጨመረ መምጣቱ የልዩ ልዩ በሽታዎችን መነሻ ከስር መሰረቱ ለማወቅ እንዲቻል ለሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ውጤታማነት የሚሰጠው ጠቀሜታ በእጅጉ ከፍተኛ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው በዛሬው እለት በኢንስትቲዩቱ የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነ ወርክሾፕ መክፈቻ ላይ ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር ሲሆን ም/ዋና ዳይሬክተሩ ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፍ ግራንት ማሸነፍ መቻሏ በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን የሚያስተዋውቅ ብሎም ተቋሙን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር ከሆኑ የምርምር አካላት ጋር በጋራ በቅንጅት ለመስራት እድሉን የሚያመቻችለት ብሎም የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያስገኝና የሀገሪቱን የምርምር ተቋም ከፍ እንዲል አጋዥ ሁኔታዎችን የሚያመቻች እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ ይህንን አለምአቀፍ የምርምር ውድድር እንዲያሸንፍ ከፍተኛ አስተዋጽ ያደረጉትን የተቋሙን ተመራማሪዎች አመስግነው ከዚህ በበለጠ ጠንክሮ በመስራት ተጨማሪ ውድድሮችን በማሸነፍ ግራንት ለማግኘትና ከሌሎች ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራትና ይበልጥ ተቋሙ እንዲተዋወቅ እድል እንደሚፈጥርለት አስረድተዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የሚተገበረው በቀጣዩ አምስት ዓመታት ሲሆን በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ሴንት ሊዊስ አማካኝነት ነው፡፡
የምርምር ጥናት ስራው የሚተገበረው በአዲስ አበባ፤ በአማራ፤ በሱማሌ፤ በጋምቤላና በሱማሌ በሚገኙ በአምስት ሆስፒታሎች ላይ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ጠቅላላ ሥራ 537 ሺህ ዶላር በጀት ተመድቦለታል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያ ሀገራችን ከአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን ከመላው አፍሪካ ለዚህ ግራንት የተመረጠች ሲሆን ልክ እንደ ሀገራችን ሁሉ የጥናትና የምርምር ስራዋቹ በቻይና እና በኔፓል ሀገራትም የሚከናወን ይሆናል፡፡
በቀጣዩ አምስት አመታት የሚተገበረው ይህ የጥናትና የምርምር ስራ በሁለት ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን በመተንፈሻ አካላት በሽታዎች እንዲሁም በሠው ልጆች፤ በሌሊት ወፍ እና በግመሎች ላይ የሚከሰት ያልታወቀ ትኩሳት መንስኤዎችን በተመለከተ ያለውን ክፍተትና የበሽታዎቹን መንስኤ ለማወቅ የሚያስችል የምርምር ጥናት ስራዎች እንደሚሰራ ለማወቅ ተችላል፡፡ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ባህሪ በተመለከተ በዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ የፕሮጀክቱ አስፈጻሚ አማካኝነት ገለጻ የተደረገ ሲሆን ዶ/ር ገረመው ጣሰው ደግሞ በቀጣዩ ስድስት ወራት የሚከናወኑ የፕሮጀክቱን ዝርዝር ተግባራትን አቅርበው ውይይቶች ተደርጎባቸዋል፡፡
በርካታ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአፍሪካ አህጉር ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ በሽታዎች ተላላፊ በሽታዎች ሲሆኑ በሌላም በኩል ደግሞ የሠውን ልጆች ከሚያጠቁት በሽታዎች ውስጥ ከ75 በመቶ በላይ ከእንሰሳት በሽታዎች ጋር ቁርኝት እንዳላቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት የሚከናወነው ይህ የጥናትና የምርምር ስራ ወደፊት በሌሎች ሆስፒታሎችም ላይ እንደአስፈላጊነቱ እንደሚተገበር ለማወቅ ተችሏል፡፡