የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት የስራ ክፍሎች በትግራይ ክልል የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት አደረጉ
በትግራይ ክልል የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ልዑካን ቡድን በቅርቡ በትግራይ ክልል የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ የጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት በክልሉ የጤና አገልግሎትን በበለጠ ለማሻሻል የተጠናከረ ድጋፍ እንዲደረግ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መለሰ የተመራ የተለያዩ የላቦራቶሪ የስራ ክፍል ኃላፊዎችን ያካተተ ቡድን በትግራይ ጤና ምርምር ኢንስቲትዩት በመገኘት የስራ ገብኝት አድርገዋል፡፡
በክልሉ የጤና ላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ለማጠናከር የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከክልሉ የጤና ምርመር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኃየሎም ካህሳይ እና ከክልሉ ላቦራቶሪ ሠራተኞች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ እንዲሁም በላቦራቶሪ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እያጋጠሙ ያሉ የላቦራቶሪ ግብዓት እጥረት፣የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ጥገና አገልግሎት፣ የተለያዩ አቅም ግንባታ ስራዎች ላይ የጋራ እቅድ ማዘጋጀት እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም ቡድኑ በአይደር አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል እና በመቀሌ ሆስፒታል በመገኘት እየተሰጡ ያሉ የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶች የተመለከተ ሲሆን የላቦራቶሪ የምርመራ አገልግሎቱን በተጠናከረ ሁኔታ መስጠት እንዲችሉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች የሚፈቱባቸው ሁኔታዎች ላይ ከሚመለከታቸው ከሆስፒታሉ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሄደ ሲሆን በተጨማሪም ቡድኑ በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት መቀሌ ቅርንጫፍ በመገኘት በመሰራጨት ላይ በሚገኙ የላቦራቶሪ ግብዓቶችን አቅርቦት ለማሻሻልና ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተገናኘ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ምክክር ከቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ አለማየሁ ገ/ማርያም ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ህረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከአጋር ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ ግምታቸው ከ20 ሚልየን ብር በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የላቦራቶሪ መሳሪዎችንና ግብዓቶች ለትግራይ ጤና ምርምር ኢንስቲትዩት ለማበርከት ተችሏል፡፡
የትግራይ ጤና ምርመር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ኃየሎም ካህሳይ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት የተደረገላቸውን የላቦራቶሪ መሳሪያዎች እና ግብዓት ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ እስካሁን በተደረገውም ድጋፍ በክልሉ ጤና ምርምር ላቦራቶሪ የኤች አይቪ የቫይረስ ልኬት እና የጨቅላ ህጻናት የኤች አይቪ ምርመራ፣የቲቢ ምርመራ፣ የኮቪድ 19 ምርመራ እና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት የተጀመረ ሲሆን የማይክሮ ባይሎጅይ፣ የቲቢ ካልቸር ምርመራ፣ የሬቢስ ምርመራ (Rabies virus diagnosis) እና ሌሎች ምርመራዎች በቅርቡ ስራ እንዲጀምሩ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተያዘም በክልልሉ ያለውን የናሙና ምልልስ እና የውጤት ቅብብሎሽ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት መቀሌ ቅርንጫፍ የስራ ኃላፊዎች ጋር ስለ አገልግሎት አሰጣጡ አሁን ያለበትን ደረጃ እና በክልሉ በሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች በሙሉ አቅም የላቦራቶሪ ናሙና ምልልስ እና የውጤት ቅብብሎሽ ስራ በተጠናከረ መልኩ በሚሰጥበት ሁኔታዎች ላይ ውይይቶች በማድረግ መግባባት ላይ ለመድረስ ተችሏል፡፡
በክልልሉ የጤና ላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶችን በሙሉ አቅም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ከፍተኛ እርብርብ የሚጠይቅ ስለሆነ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እያደረገ ያለውን ድጋፍ በበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ የጤና ምርመር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኃየሎም ካህሳይ እና ሰራተኞች ጠይቀዋል፡፡