የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት በደቡብ እና በሲዳማ ክልሎች
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት በደቡብ እና በሲዳማ ክልሎች ከሚገኙ ከተለያዩ ወረዳዎች ተውጣጥተው መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ለ3 ወራት ወስደው ላጠናቀቁ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ግንቦት 25/2015 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ በተዘጋጀው 3ኛው ዙር ማጠቃለያ ስልጠና ላይ የእውቅና ሰርተፍኬት ሰጠ፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ በሕብረተሰብ ጤና ላይ ችግር የሚፈጥሩ በሽታዎችና ወረርሽኞችን ቀድሞ በመለየት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስልጠና ለጤና ባለሙያዎች በመስጠትና አቅም በመገንባት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚከሰቱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታስቦ የሚሰጥ ስልጠና ነው፡፡
ዶ/ር ሲሳይ ተመስገን የኢንስቲትዩቱ የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት የአቅም ግንባታ ቡድን አስተባባሪ የስልጠናወን የማጠቃለያ ንግግር ባደረጉባት ወቅት እንደተናገሩት ስልጣኞች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በሚሰሩበት የጤና ተቋማት ተግባራዊ በማድረግ የተለያዩ የጤና ችግሮችን በመፍታት ትልቁን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
የሲዳማ ክልል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ በድሉ ባዴጎ በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎች ለ3 ወራት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ባለሙያዎቹ ከሚሰሯቸው ስራዎች ጋር ቀጥታ የሚገናኝና የተግባር ስልጠና በመሆኑ የሚሰሩትን ስራ በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ዶ/ር ታጠቅ ቦጋለ የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች የሪጂናል ቴክኒካል አስተባባሪም በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ ተግኝተው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀት፣ የበሽታ ቅኝት መረጃ አሰባሰብ፣ እና በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን የመለየት ስራ እንዲሁም ወረርሽኝ በአንድ አካባቢ ሲከሰት ቅድሚያ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጉዳዮች፣ ሳይንሳዊ ገለጻ፣ የወረርሽኝ ሪፖርት አቀራረብ፣ መካተት ያለባቸውን ጉዳዮች፣ የወረርሽኝ መንስኤ እና ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍል የትኛው ነው የሚሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች ለባለሙያዎቹ በስፋት መሰጠቱን ከስልጠናው አስተባባሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡
ሰልጣኝ ባለሙያዎች በስራ ቦታ የተሰጧቸውን የፊልድ ፕሮጀክት አጠናቀው በጽሁፍና በፊት ለፊት ገለጻ አቅርበው የተመዘኑ ሲሆን አጠቃላይ የተሰጣቸው ስልጠና ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን የእለት ከእለት የጤና አገልግሎቶች ውጤታማ እና በተሻለ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ እውቀት እንዳስጨበጣቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአጠቃላይ ስልጠናውን ተከታትለው እና ተሳትፈው ያጠናቀቁ አማካይ ውጤታቸው 70 ከመቶ በላይ ያስመዘገቡ 34 የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡