የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሲዲሲ ግሎባል እርዳታዎችን አገኘ
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ክብርት ትሬሲ አን ጃኮብሰን የተመራ ቡድን የስራ ጉብኝት አደረጉ፡፡ ክብርት አምባሳደርዋ የኢንስቲትዩቱን የድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከልን፣ ላቦራቶሪዎችን (ኢንፍሎዌንዛ፣ ቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪ) እና በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘውን CDC-ኢትዮጵያ ቢሮ የጎበኙ ሲሆን ለኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የላቦራቶሪ ግብአቶች ድጋፍ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላለፉት በርካታ አመታት ከሲዲሲ ግሎባል (CDC Globa)l ጋር በቅርበት እየሰራ የቆየ ሲሆን ሲዲሲ ግሎባል ለኢንስቲትዩቱ ለሕብረተሰብ ጤና አገልግሎት የሚውሉ የመሠረተ ልማት ስራዎችን በማገዝ፣ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማጠናከር ደረጃ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህም ነባር የሆኑትን The U.S. President’s Emergency Plan for AIDS Relief (PEPFAR) እና The Global Health Security Agenda (GHSA) ፕሮግራሞች ማጠናከሪያ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሥነ-ሥርአቱ ላይ ሲዲሲ ግሎባል የሀገሪቷን የጤና ስርዓት ለማጎልበትና ለማዘመን እያደረገ ስላለው እገዛና እርዳታ ምስጋናቸውን አቅርበው በተለይ የበሽታዎችን መለየት፣ መከላከል እና መቆጣጠር እንዲሁም ለሚከሰቱ በሽታዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የመሠረተ ልማት ስራዎችን በከፍተኛ መጠን መዋዕለ ነዋይ ለሚደረጔ ድጋፍ ለአሜሪካን መንግሥት እና ህዝብ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በሥነ-ሥርአቱ ላይ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በሲዲሲ ግሎባል መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ወዳጅነት እና ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሁለቱም ተቋማጽ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሙሉ እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል።