የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ጽ/ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ውይይት አካሄዱ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የዓለም ጤና ድርጅት ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ትብብር ይበልጥ በማጎልበት በቀጣይ በቅርበት ለመስራት የሚያሰችላቸውን ውይይቶች አካሄዱ፡፡
ዶ/ር ቦሩማ ሀማ ሳምቦ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ የተመራው ቡድን ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ እና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንዲሁም ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ፍሬያማ የሆነ ውይይቶችን አከናውነዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ለሀገራችን ልዩ ልዩ ጤና ነክ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት የሚሰጠው ምላሽና ተቋሙም የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑ በውይይቱ ወቅት የተገለፀ ሲሆን ለአብነት ያህልም በተለይ እንደ ኮቪድ-19 እና ድርቅ በሚያጋጥሙበት ወቅት አለም አቀፉ ተቋም እየሰጠ ያለው እገዛ የጎላ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ለእዚህም የኮሌራ በሽታን በአጥጋቢ ሁኔታ በመከላከል ረገድ፣ ውጤታማ የሆነውን የክትባት ዘመቻ በመደገፉ በኩል፣ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከልን በማጠናከር አኳያ፣ ልዩ ልዩ የህክምና ግብአቶችን በማሟላት፣ ለዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ቅድመ መከላከል ዝግጁ በመሆን እና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ እየተደረጉ ያሉ ልዩ ልዩ ድጋፎች ተወስተዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ወረርሽኝ በሽታዎች ሲከሰቱ በማስተባበርና ምላሽ በመስጠቱ በኩል ከአህጉራችን አፍሪካ በጥሩ ተሞክሮዋ የምትጠቀስ መሆኗ የተጠቀሰ ሲሆን በተለይ ሁለቱ ተቋማት የጋራ ትብብርና ርብርቦሽ በማድረጋቸው እንደ ኢንፌሌንዛ፣ፖሊዮ እና ኩፍኝ የመሳሰሉትን በሽታዎች አጥጋቢ በሆነ መልኩ ለመቆጣጠር እንደተቻለ ተብራርቷል፡፡ በመሆኑም የሀገራችን የጤናው ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ ይሆን ዘንድ የአለም ጤና ድርጅት ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡