የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ በጤናው ዘርፍ
ዘርፍ ለማህበረሰቡ የሚሰጡት አገልግሎቶች በጥናትና ምርምር የተደገፉ ብሎም ዘመኑን የዋጁ ይሆኑ ዘንድ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ተፈራረሙ፡፡
የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ሠነዱ ሁለቱ ተቋማት በትምህርት፤ በጥናትና ምርምር፤ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት፤ በድንገተኛ አደጋና በሽታዎች ላይ እንዲሁም በስታፍ ህክምናና ሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ሁለቱ ተቋማት በጋራና በቅንጅት መስራታቸው በጤናው ዘርፍ የተቀመጠውን እቅድና ግብ ለማሳካት ብሎም ለተገልጋይ ህዝባችን የምንሰጠውን ግልጋሎቶች ይበልጥ ተደራሽ፤ አርኪና ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ወንድማገኝ ገዛኸኝ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ፕሮቮስት በበኩላቸው ኮሌጁ የሚያደርገውን የጥናትና ምርምር እንዲሁም በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ አብሮ በጋራ መስራት መቻሉ ለህብረተሰቡ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ሲሉ አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ እና የህክምና ኮሌጁ ለአንድ ሕብረተሰብ ጤና በጋራ የቆሙ፣ ለአንድ ሚኒስቴር መ/ቤት ተጠሪ የሆኑ እህትማማች ተቋማት ሆነው ለሕብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ከመሆናቸውም በላይ ከስራ ትስስራቸው አኳያ በርካታ ተግባራትን በጋራ በማከናወን ላይ የሚገኙ ተቋማት ናቸው፡፡