የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአፍሪካ ሶሳይቲ ላቦራቶሪ ሜድስን (African Society for Laboratory Medicine)
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአፍሪካ ሶሳይቲ ላቦራቶሪ ሜድስን (African Society for Laboratory Medicine) ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የጤና ላቦራቶሪዎች አደረጃጀት፣ ሥርዓትና የምርመራ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ አሰሳና ምዘና (LabCOP Integrated assessment score card) ለማከናወን በአዲስ አበባ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ከህዳር 15/2015 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣይ ሁለት ቀን የሀገሪቱ የጤና ላቦራቶሪዎች ያሉበትን ደረጃ እየገመገመ ይገኛል፡፡
የጤና ላቦራቶሪ ሥርዓቱን በማደራጀት የተቀናጀ የምርመራ አገልገሎት እንዲሰጡ ለማስቻል በ2008 በሞዛምቢክ እና በ2015 እ.አ.አ በሴራሊዮን በተደረጉት ስብሰባዎች የአፍሪካ የጤና ላቦራቶሪዎችን አደረጃጀትና ዕድገትን አስመልክቶ ያወጡትን የማፑቶ ስምምነት ተግባራዊ ካደረጉ አገራት መካካል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ከማፑቶ ስምምነት ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የጤና ላቦራቶሪ ምርመራ ቴክኖሎጂዎች በተጠናከረ መልኩ ሥራ ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ከአንድ ዓይነት በላይ ምርመራ አገልገሎት መስጠት የሚችሉ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችን (Multiplex testing technology) ሥራ ላይ በሰፊው እየተተገበሩ ሲሆን በዚህም መሠረት ሀገራት ያላቸውን ዝግጅት እንዲሁም አንድ ጤና ትስስር (One Health network) አተገባበር አንፃር የጤና ላቦራቶሪዎች ያላቸውን ትስስር እና ጥንካሬ በዋናነት በዚህ ግምገማ ከአፍሪካ ሶሳይቲ ላቦራቶሪ ሜድስን በመጡ ባለሙያዎች በሦስተኛ አካል የሚፈተሽ ይሆናል፡፡
የክልል ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መለሰ እንደገለጹት ይህ የተቀናጀ የጤና ላቦራቶሪዎች አደረጃጀት፣ ሥርዓትና የምርመራ አገልግሎት አሰጣጥን ምዘና በጤና ላቦራቶሪ ዘርፉ ያለንን አቅም ከማወቅ በተጨማሪ የሚገኙ ክፍተቶችን ለይቶ በማወቅ የማሻሻያ እቅዶች በማዘጋጀት ከሁሉም ባለድርሻ አካላቶችና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተግባራዊ ለማድረግ እጅግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ቀድማ እንደ ሥርዓት እየተገበረች ያለች ሀገር በመሆኗ አሁን በላቦራቶሪ ዘርፍ እየመጡ ያሉ አዳዲስ አሰራሮችን በተጠናከረ መልኩ ወደ ሥራ ለማስገባት አስቸጋሪ እንደማይሆን እንዲሁም የተቀናጀ የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት አሰጣጥ ምዘና ኢትዮጵያን ጨምሮ እስካሁን በሰባት የአፍሪካ ሀገራት ላይ እንደተሠራ መሆኑን አቶ ዳንኤል አያይዘው ተናግረዋል፡፡